መፍቻ

በዚህ መጽሐፍ የተካተቱትን ምእራፎች ስናነብ ከምናገኛቸው ታክኒካዊ ስያሜዎች መካከል የተወሰኑት እዚህ በአጭሩ ተተርጉመዋል።

 • አቫስት (Avast): በነጻ የሚገኝ ጸረ ቫይረስ መሣሪያ

 • መሠረታዊ የግብአት/ውጤት ሲስተም- ባዮስ (Basic Input/Output System-BIOS): የኮምፒውተር ሶፍትዌር የመጀመሪያው እና መሠረታዊው ደረጃ ነው። ባዮስ የኮምፒውተራችንን ሐርድዌር ደኅንነት ለማረጋገጥ የሚረዱ የተለያዩ አማራጮችን ይሰጠናል፤ ኮምፒውተራችን ሲከፈት በይለፍ ቃል ብቻ እንዲገባ ማድረግ ከእነዚህ አንዱ ነው።

 • ጥቁር መዝገብ (Blacklist): በገዳቢ የክልከላ ፖሊሰ የታገዱ ድረ ገጾች እና ሌሎች የኢንተርኔት አገልግሎቶች ዝርዝር ነው።

 • ብሉቱዝ (Bluetooth): ከሞባይል እና ከባለመስመር ስልኮች በአጭር ርቀት ዳታ ለመላላክ የሚያስችል ገመድ አልባ የግንኙነት ደረጃ ነው። ቡሉቱዝ ዳታ ለመለዋወጥ አጭር ሞገዶችን ይጠቀማል።

 • ቡቲንግ (Booting): ኮምፒውተርን ሥራ ማስጀመር ወይም ማስነሳት ነው።

 • ሲክሊነር (CCleaner): በነጻ የሚገኝ ሶፍትዌር ነው። በቅርብ በተጠቀምንባቸው ፕሮግራሞችና በዊንዶውስ ኦፐሬቲንግ ሲሰተም አማካኝነት በሐርድ ዌራችን ላይ የተተዉ ጊዜያዊ ፋይሎችን ዱካ የሚያሳዩ መረጃዎችን የሚያጸዳ ሶፍትዌር ነው።

 • ሲዲ በርነር (CD Burner): በባዶ ሲዲዎች ላይ መረጃ ለመጻፍ የሚችል የኮምፒውተር ድራይቭ ነው። ዲቪዲ በርነር (DVD burners) በተመሳሳይ መንገድ በባዶ ዲቪዲዎች ላይ ይጽፋል። ሲዲ-አርደብሊው (CD-RW ) እና ዲቪዲ-አርደብሊው ድራይቮች (DVD-RW drives) ደግሞ በሲዲ/ዲቪዲ ላይ የተጻፈውን አጥፍተው ከአንድ ጊዜ በላይ መልሰው መጻፍ ይችላሉ።

 • ሰርከምቬንሽን (Circumvention): በኢንተርኔት አፈና የታገዱ ድረ ገጾችን እና የኢንተርኔት አገልግሎቶችን ለማግኘት እገዳውን ማለፍ።

 • ክሌም ዊን (Clam Win): ለዊንዶውስ የተሠራ የኤፍኦኤስኤስ ጸረ ቫይረስ

 • ኮቢያን ባክአፕ (Cobian Backup): የኤፍኦኤስኤስ የመጠባበቂያ ማከማቻ መሣሪያ ነው። የቅርብ ጊዜዎቹ የኮቢያን አይነቶች ምንጫቸው የማይገለጽ ነገር ግን በነጻ የሚገኙ ናቸው፤ የቀድሞዎቹ ግን በኤፍኦኤስኤስ ብቻ የሚለቀቁ ነበሩ።

 • ኮሞዶ ፋየርዎል (Comodo Firewall): ምንጩ (ውስጣዊ መዋቅሩ) ለምርመራ ክፍት የሆነ፣ በነጻ የሚገኝ የፋየርዎል መሣሪያ ነው።

 • ኩኪ (Cookie): የኢንተርኔት ማሰሻ (browser) በኮምፒውተር ላይ የሚተዋቸው የጎበኘነውን ድረ ገጽ እና ተያያዥ መረጃዎችን መዝግቦ የሚይዝ አነስተኛ ፋይል ነው።

 • ዲጂታል ፊርማ (Digital signature): ኢንክሪፕሽንን በመጠቀም አንድ ፋይል ወይም መልእክት ከትክክለኛው ሰው የተላከ መሆኑን የማረጋገጫ መንገድ

 • የዶሜይን ስም (Domain name): በቃላት የሚገለጽ የድረ ገጽ ወይም የኢንተርኔት አገልግሎት አድራሻ፤ ለምሳሌ securityinabox.org

 • ኢንክሪፕሽን (Encryption): የተራቀቀ ሒሳባዊ ስሌትን በመጠቀም ኢንክሪፕት (encrypt) ማድረግ፤ ትክከለኛው መረጃ ማለትም የይለፍ ቃል ወይም የኢንክሪፕሽን ቁልፍ (encryption key) ያለው ሰው ብቻ ኢንክሪፕት የተደረገውን መረጃ ዲክሪፕት ማድረግ/መክፈት (decrypted) እንዲችል የሚያደርግ

 • ኢንጂሜይል (Enigmail): የታንደርበርድ የኢሜይል ፕሮግራም አጋዥ መሣሪያ (add-on) ነው፤ ተጠቃሚዎቹ ኢንክሪፕት የተደረገ ወይም በዲጂታል ፊርማ የታተመ መልእክት ለመላክና ለመቀበል የሚያስችል

 • ኢሬዘር/መደምሰሻ (Eraser): ከኮምፒውተር ወይም ከሌሎች ተንቀሳቃሽ የመረጃ ማከማቻዎች ላይ የሚገኝ መረጃን በአስተማማኝ እና በዘላቂነት ከነጭራሹ ለማጥፋት (delete) የሚያስችል መሣሪያ

 • ፋየርፎክስ (Firefox): የታወቀ የኤፍኦኤስኤስ ማሰሻ (FOSS Web browser) ነው፤ ከማይክሮሶፍት ማሰሻ “ከኢንተርኔት ኤክስፕሎረር” የተለየ አማራጭ ነው።

 • ፋየርዎል (Firewall): ኮምፒውተርን አስተማማኝ ካልሆኑ የኢንተርኔት እና የቤት ውስጥ መረቦች ግንኙነት የሚጠብቅ መሣሪያ ነው።

 • ነጻና ቀመሩ የሚታይ ሶፍትዌር- ኤፍኦኤስኤስ (Free and Open Source Software-FOSS): ያለክፍያ በነጻ የሚገኙ እንዲሁም ተጠቃሚዎች የሶፍትዌሮቹን አሠራር እንዲመረምሩ፣ እንዲፈትሹ፣ እንዲያሻሽሉና ለሌሎች አሳልፈው እንዲሰጡ የሚፈቅዱ ሶፍትዌሮች ምድብ

 • ፍሪዌር (Freeware): በነጻ የሚገኙ፣ ነገር ግን ተጠቃሚዎች መሠረታዊ የፈጠራ አወቃቀሩን (source code) እንዳያገኙ ሕጋዊና ቴክኒካዊ ክልከላዎችን የሚያደርጉ ሶፍትዌሮች

 • ጂኤንዩ/ሊኑክስ (GNU/Linux): የኤፍኦኤስኤስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ነው፤ ለማይክሮሶፍት ዊንዶውስ አማራጭ ሲስተም ነው።

 • ጂፒኤስ (Global Positioning System -GPS): በስፔስ/ምህዋር ላይ መሠረት ያደረገ በሳተላይት በመታገዝ ቦታንና ጊዜን ለመለየት የሚያስችል፤ በማንኛውም የአየር ሁኔታ፣ በየትኛውም የምድራችን ወይም በአቅራቢያዋ ባሉ ቦታዎች የሚሠራ፤ ከሞላ ጎደል በምንም ነገር የማያደናቀፍ ከሰማይ ከፍታ ለመመልከት የሚያስችል የሳተላይት መመልከቻ ነው።

 • ሐከር/ሰባሪ (Hacker): በዚህ አገባቡ፣ ከርቀት ኮምፒውተራችንን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ወይም ስሱ መረጃዎቻችንን ለመስረቅ የሚሞክር ወንጀለኛ

 • የኢንተርኔት ፕሮቶኮል አድራሻ-(አይፒ አድራሻ) (Internet Protocol address -IP address): ማንኛውም ኮምፒውተር ከኢንተርኔት ጋራ ሲገናኝ የሚሰጠው ልዩ መለያ

 • ኢንተርኔት አገልግሎት ሰጪ (አይኤስፒ) (Internet Service Provider-ISP): የኢንተርኔት ግንኙነት መስመር አገልግሎት የሚሰጥ ኩባንያ ወይም ድርጅት። የብዙ አገሮች መንግሥታት ኢንተርኔትን በጣም ይቆጣጠራሉ፤ እነዚህን አገልግሎት ሰጪዎች (አይኤስፒ) በመጠቀምም የኢንተርኔት ክልከላ፣ ስለላ እና እገዳ ያደርጋሉ።

 • ኢንፍራሬድ ዳታ አሶሲዬሽን (Infrared Data Association) (ኢርዳ/IrDA): በአጭር ርቀት የኢንፍራሬድ ስፔክተረም ጨረሮችን በመጠቀም መረጃ/ዳታ ለመለዋወጥ የሚያስችል ገመድ አልባ የግንኙነት መንገድ ነው። በዘመናዊ መገልገያዎች ውስጥ ኢርዳ/IrDA በብሉቱዝ ተተክቷል።

 • ጃቫ አፕሊኬሽንስ (Java Applications) (አፕልትስ/Applets): በብዙ ኦፕሬቲንግ ሲስተሞች ላይ የሚሠሩ አነስተኛ ፕሮግራሞች ናቸው። ብዙውን ጊዜ በድረ ገጾች ውስጥ የተሻሻሉ አገልግሎቶችን (functionalities) ለመስጠት ጥቅም ላይ ይውላሉ።

 • ኪይሎገር (Keylogger): ለስለላ ተግባር የሚውል የስፓይዌር አይነት ነው፤ በኮምፒውተሩ የመተየቢያ ገበታ (keyboard) ላይ የነካናቸውን/የተጫንናቸውን ቁልፎች/ፊደሎች በሙሉ መዝግቦ ለሦስተኛ ወገን ይልካል። ኪይሎገሮች የኢሜይሎችን እና የይለፍ ቃሎችን ለመስረቅ በብዛት ጥቅም ላይ ይውላሉ።

 • ኪፓስ (KeePassX): የአስተማማኝ የይለፍ ቃል ማከማቻ (database) ፍሪዌር ነው።

 • ላይቭ-ሲዲ (LiveCD): ኮምፒውተር ለጊዜው ዘወትር ከሚሠራበት በተለየ ኦፐሬቲንግ ሲስተም እንዲሠራ የሚያስችል ሲዲ

 • ማልዌር (Malware): ቫይረሶች (viruses) ፣ ስፓይዌር (spyware) ፣ ትሮጃኖች (Trojans) እና የመሳሰሉት ጎጂ ሶፍትዌሮች የጥቅል ስም

 • ኔሞኒክ መሣሪያዎች (Mnemonic device): በጣም ውስብስብ የሆኑ የይለፍ ቃሎችን በቀላሉ ለማስታወስ የሚያስችል ዘዴ

 • ኖስክሪፕት (NoScript): ባልተለመዱ ድረ ገጾች ውስጥ ተሰውረው የሚመጡ አደገኛ ፕሮግራሞች እንዳያጠቁን የሚከላከል የፋየርፎክስ ማሰሻ (Firefox browser) የደኅንነት አጋዥ መሣሪያ ነው

 • ኦፍ ዘ ሪከርድ/የማይመዘግብ (Off the Record) (ኦቲአር/OTR): የፒድጂን (Pidgin) ፈጣን መልእክት ፕሮግራም ኢንክሪፕሽን ማድረጊያ

 • ፒስፋየር (Peacefire): ይህን ነጻ አገልግሎት ለማግኘት የተመዘገቡ ተጠቃሚዎች በየጊዜው የሚዘጋጁ የኢንተርኔት ሳንሱርን ለማለፍ የሚያስችሉ የሰርከምቬንሽን ፕሮክሲዎች (circumvention proxies) ዝርዝር በኢሜይሎቻቸው ይላክላቸዋል

 • አካላዊ ስጋት/አደጋ (Physical threat): የኮምፒውተራችን ሐርድዌር በሌሎች ሰዎች እጅ በመውደቁ የተነሣ ስሱ መረጃዎቻችንን ለአደጋ የሚጋልጥ ስጋት፤ ወይም ሌላ አካላዊ አደጋ ለምሳሌ መሰበር፣ የተፈጥሮ አደጋ እና ድንገተኛ ጥፋት

 • ፒድጂን (Pidgin): የኤፍኦኤስኤስ የፈጣን መልእክት መሣሪያ ኢንክሪፕት ለማድረግ የሚጠቀምበት “ኦፍ ዘ ሪከርድ/የማይመዘግብ (Off the Record)” (ኦቲአር/OTR) የተባለው መርጃ አካል

 • ፕሮክሲ (Proxy): የኢንተርኔት ሳንሱርን ወይም እገዳን ለማለፍ የሚያስችል በእኛ እና በምንፈልገው ድረ ገጽ/አገልግሎት መካከል ሆኖ የሚያገናኝ አገልግሎት ነው። ለሕዝብ ክፍት የሆኑ ፕሮክሲዎች አሉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ በግል የተጠቃሚ ስምና በይለፍ ቃል የምናገኛቸው ናቸው። ሆኖም ደኅንነታቸው ሙሉ በሙሉ የተጠበቁት ፕሮክሲዎች አንዳንዶቹ ብቻ ናቸው፤ ይህም ማለት እነዚህ ፕሮክሲዎች በእኛ ኮምፒውተር እና በፕሮክሲው በኩል በምናገኘው የኢንተርኔት አገልግሎት መካከል የሚኖረውን ግንኙነት ኢንክሪፕት በማድረግ ምሥጢራዊነቱን ያረጋግጣል ማለት ነው።

 • ፕሮፕሪታሪ ሶፍትዌር (Proprietary software): የነጻ እና መሠረታቸው/ቀመራቸው ክፍት የሆነ ሶፍትዌሮች (Free and Open-Source Software) (ኤፍኦኤስኤስ/FOSS) ተቃራኒ ነው። እነዚህ አፕሊኬሽኖች በአብዛኛው በግዢ/ክፍያ የሚገኙ ናቸው፤ ሆኖም በጣም ገዳቢ በሆነ ቅድመ ሁኔታ በነጻ ሊገኙ ይችላል።

 • ራይዝአፕ (RiseUp): በዌብሜይል ወይም ሞዚላ ተንደርበርድን (Mozilla Thunderbird) በመሳሰሉ አገልግሎቶች የሚገኝ ደኅንነቱ የተጠበቀ የኢሜይል አገልግሎት ነው። በአቀንቃኞች/በቀስቃሾች በብዛት ጥቅም ላይ ይውላል፤ ፈጣሪዎቹም እነርሱው ናቸው።

 • ራውተር (Router): በቢሮ ውስጥ የሚገኙ ኮምፒውተሮች ከአካባቢ መረብ (local networks) ጋራ የሚገናኙበት መሣሪያ፤ ከኢንተርኔት ጋራም የሚገናኙት በዚሁ ነው። Switches (ስዊች/ማዞሪያ)፣ ጌትዌይ (gateways) እና ሐቦች (hubs) እና መሰሎቻቸውም ተመሳሳይ አገልግሎት ይሰጣሉ፤ ተገቢው መሣሪያ የተገጠመላቸው ኮምፒውተሮች በገመድ አልባ ነጥቦች (access points) እንዲሁ በመረብ ይገናኛሉ።

 • አስተማማኝ የይለፍ ቃል መዝገብ (Secure password database): የይለፍ ቃሎችን ኢንክሪፕት አድርጎ የሚያከማች እና በአንድ እናት/ማስተር የይለፍ ቃል የሚቆለፍ መሣሪያ

 • ሴክዩር ሶኬት ሌየር (Secure Sockets Layer) (ኤስኤስኤል/SSL): በኮምፒውተራችን እና በምንጎበኘው ድረ ገጽ ወይም የኢንተርኔት አገልግሎት መካከል ያለውን ግንኙነት ኢንክሪፕት በማድረግ ደኅንነቱን የተጠበቀ የሚያደርግ ቴክኖሎጂ። በኤስኤስኤል በኩል ከድረ ገጾች ጋራ ስንገናኝ የድረ ገጹ አድራሻ መግቢያ HTTP በመሆን ፋንታ HTTPS ይሆናል።

 • የደኅንነት/ሴኩዩሪቲ ሰርተፊኬት (Security certificate): አስተማማኝ ደኅንነት ያላቸው ድረ ገጾች እና የኢንተርኔት አገልግሎቶች ትክክለኛና ታማኝ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው። ማሰሻችን (ብራውዘር) የደኅንነት/ሴኪዩሪቲ ሰርተፊኬቱን (security certificate) እውነተኛነት እንዲለይ ለማስቻል ግን ድረ ገጹ ወይም አገልግሎቱ ከታመኑ ድርጅቶች ዲጂታል ፊርማ (digital signature) በክፍያ ማግኘት አለባቸው። ይህንን ዋጋ ለመክፈል የማይችሉ ወይም የማይፈልጉ አንዳንድ ድረ ገጾች/ድርጅቶች አሉ። ሆኖም ከፍለው ማረጋገጫ ሰርተፊኬቱን ያገኙትንም ቢሆን ስንከፍታቸው የተሳሳተ መልእክት የምንናገኝበት ጊዜ አለ።

 • የደኅንነት ፖሊሲ (Security policy): በጽሑፍ የሰፈረ፣ ድርጅቶች ራሳቸውን ከተለያዩ አደጋዎችና ስጋቶች ለመጠበቅ የሚችሉባቸውን መንገዶች፣ እንዲሁም አደጋዎች ቢደርሱ ሊወሰዱ የሚገባቸውን እርምጃዎች አካቶ የያዘ ሰነድ

 • ማሰሪያ ገመድ (Security cable): ላፕቶፕ እና ሌሎች ሐርድዌሮች እንዲሁም ከኮምፒውተሩ ውጭ የሚቀመጡ ነገሮች (external hard drives) እንዳይሰረቁ ከጠረጴዛ ወይም ከግድግዳ ጋራ ለማሰር የሚጠቅም ለዚሁ ተብሎ የተሰራ የሚቆለፍ ገመድ/ማሰሪያ። በዚህ መታሰር የሚችሉ የጠረጴዛ ላይ (ዴስክቶፕ) ኮምፒውተሮችም አሉ።

 • ሰርቨር (Server): ለሌሎች ኮምፒውተሮች አገልግሎት ለመስጠት ሲባል ከኢንተርኔት ጋር ተገናኝቶ ሳይጠፋ የሚቀመጥ ኮምፒውተር ነው። ለሌሎቹ ኮምፒውተሮች የሚሰጠው አገልግሎት ድረ ገጽን ማስተናገድ ወይም ኢሜይሎችን ለመላክና ለመቀበል እንዲችሉ ማድረግ ወዘተ ሊሆን ይችላል።

 • ሲም ካርድ (SIM card): ከአንድ የቴሌፎን ኩባንያ አገልግሎት ለማግኘት የሚያስችል፣ በሞባይል ውስጥ በተሠራለት ቦታ ሊገባና ሊወጣ የሚችል አነስተኛ ካርድ ነው። ሲም ካርድ ላይ የስልክ ቁጥሮችን እና መልእክቶችን ማጠራቀም ይቻላል።

 • ስካይፕ (Skype): ከሌሎች የስካይፕ ተጠቃሚዎች ጋራ ያለምንም ክፍያ ለመነጋገር እንዲሁም በክፍያ ወደ ስልኮች ለመደወል የሚያስችል ነጻ/ፍሪዌር “ቮይስ ኦቨር አይፒ” (Voice over IP (VoIP)) ሶፍትዌር ነው። ስካይፕን የሚያስተዳድረው ኩባንያ በስካይፕ ተጠቃሚዎች መካከል የሚደረግ ግንኙነት ኢንክሪፕት ይደረጋል፤ ስለዚህም አስተማማኝ ነው ይላል። ሆኖም የሶፍትዌሩ መሠረታዊ አወቃቀር በምሥጢር የተያዘ መሣሪያ (closed-source tool) በመሆኑ ይህንን በገለልተኛ ወገኖች ለማረጋገጥ አይቻልም፤ ብዙ ሰዎች ግን ነገሩ እውነት ነው ብለው ያምናሉ። ስካይፕ ፈጣን መልእክቶችን ለመለዋወጥም ያስችላል።

 • የመሠረታዊ ቀመር ኮድ (Source code): የኮምፒውተር ፕሮግራም ፈጣሪዎች አንድን ሶፍትዌር ሲፈጥሩ መጀመሪያ የሚያስቀምጡት የመሠረታዊ ቀመር ኮድ ነው። የመሠረታዊ ቀመር ኮድ አንድ መሣሪያ/ሶፍትዌር እንዴት እንደሚሠራ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ ይሁን ወይም ደግሞ ጎጂ ያሳውቃል።

 • ስፓይቡት (Spybot): ኮምፒውተርን የሚፈትሽ (scan የሚያደርግ)፣ ከስፓይዌር የሚጠብቅ እና ከተገኘም የሚያጠፋ ነጻ/ፍሪዌር ጸረ ማልዌር መሣሪያ።

 • ስቴጋኖግራፊ (Steganography): ስሱ መረጃዎችን በመሰወር ሌላ ነገር መስለው እንዲታዩ በማድረግ ትኩረት እንዳይስቡ የሚያደርግ ነው።

 • ስዋፕ ፋይል (Swap file): የኮምፒውተር አቅም/ፍጥነት እንዲሻሻል ለማድረግ ሲባል መረጃዎች ብዙ ጊዜ የሚቀመጡበት (ሴቭ የሚደረግበት) ፋይል ነው፤ መረጃዎቹ ስሱ ሊሆኑ ይችላሉ።

 • ታንደርበርድ (Thunderbird): በርካታ የደኅንነት መጠበቂያ አገልግሎት አይነቶች ያሉት የኤፍኦኤስኤስ ኢሜይል ፕሮግራም፤ የኢኒጂሜይል ኢንክሪፕሽን አጋዥ መሣሪያንም አካቶ ይይዛል።

 • ቶር (Tor): የኢንተርኔት ሳንሱርን ለማለፍ እና የምንጎበኛቸውን ድረ ገጾች እና የኢንተርኔት አገልግሎቶች ለመከታተል የሚሞክር ቢኖር ከእርሱ እንድንሰወር የሚያደርገን መሣሪያ ነው። በተጨማሪም የምንጎበኛቸው ድረ ገጾች ራሳቸውን ያለንበትን ቦታ እንዳያውቁት ያደርጋል።

 • VeraCrypt: ስሱ መረጃዎችን ደኅንነቱ በተጠበቀ መንገድ ለመደበቅ የሚያስችል፣ ፋይሎችን ኢንክሪፕት የሚያደርግ የኤፍኦኤስኤስ መሣሪያ ነው።

 • አንዴሊት ፕላስ (Undelete Plus): በስሕተት የተደመሰሱ (delete) መረጃዎችን አንዳንድ ጊዜ መልሰን እንድናገኛቸው (restore) የሚረዳ ፍሪዌር (ነጻ ሶፍትዌር)

 • የማይቋረጥ የኀይል አቅርቦት (Uninterruptable Power Supply) (ዩፒኤስ/UPS): በጣም ወሳኙ የኮምፒውተር ሐርድዌር በኀይል አቅርቦት መቋረጥ እንዳይቆም ወይም መቋረጥ ሲኖር ጊዜ አግኝቶ በተገቢው መንገድ እንዲዘጋ ለአጭር ጊዜ ኅይል የሚያቀርብ ቁስ

 • ቮትሌትሱት 2ጎ (VautletSuite 2Go): ኢንክሪፕት የተደረገ ፍሪዌር የኢሜይል ፕሮግራም

 • ቮይስ ኦቨር ኤይፒ (Voice over IP) (ቪኦአይፒ/VoIP): በኢንተርኔት የድምጽ ግንኙነት ለማድረግ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው፤ ግንኙነቱን ለማድረግ ግን ሁለቱም የቪኦአይፒ/VoIP ተጠቃሚ መሆን አለባቸው። ከኢንተርኔት ወደ ስልክ የሚደረገው የድምጽ ግንኙነትም የሚሠራው በዚሁ ቴክኖሎጂ ነው።

 • ነጭ መዝገብ (Whitelist): ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል እንዲታዩ/እንዲጎበኙ የተፈቀዱ ድረ ገጾችና የኢንተርኔት አገልግሎቶችን ዝርዝር ነው፤ በተቃራኒው የሚታገዱ ድረ ገጾች ዝርዝር ይኖራል።

 • ዋይፒንግ (Wiping): መረጃን በአስተማማኝ መንገድ እስከወዲያኛው የማጥፋት ሒደት

 • ዩር ፍሪደም (Your Freedom): በግል ፕሮክሲ በኩል ከኢንተርኔት ጋራ በመገናኘት የኢንተርኔት ክልከላን ወይም ማጥለልን ለማለፍ የሚያስችል ፍሪዌር የሰርከምቬንሽን መሣሪያ ነው። የምንጠቀምበት ዩር-ፍሪደም በተገቢው መንገድ እንዲሠራ ተደርጎ ከተስተካከል ከፕሮክሲዎቹ ጋራ የምናደርገው ግንኙነት ራሱ ኢንክሪፕት ስለሚደረግ ምሥጢራዊነቱ የተጠበቀ ይሆናል።