6. ስሱ መረጃዎችን በጥንቃቄ ማጥፋት የሚቻለው እንዴት ነው?

Updated2010

መመሪያው በወቅቱ አልተሻሻለም፤ በቅርቡ ይሰረዛል

እስካሁን በነበሩት ምእራፎች ስሱ መረጃዎችን እንዴት በምሥጢር መጠበቅየምንችልባቸውን አስፈላጊ መሣሪያዎች እና ልማዶች ተመልክተናል። ለመሆኑ አንድን ስሱ መረጃ የማንፈልግበት ጊዜና ሁኔታ ቢፈጠር፣ ስለዚህም እስከወዲያኛው ለማጥፋት ብንፈልግ ምንድን ነው የምናደርገው? ለምሳሌ በመጠባበቂያ ክምችታችን (በባክአፕ) የያዝነው አንድ ስሱ መረጃዎችን የያዘ ፋይል ሁለተኛ ቅጂ በቂ እንደሆነ ብናስብና እናት ቅጂውን ከነጭራሹ ማጥፋት ወስነናል እንበል። ይህን ለማድረግ ያለን የተሻለ አማራጭ ምንድን ነው? እንዳለመታደል ሆኖ የዚህ ጥያቄ መልስ ቀላልና ቀጥተኛ ላይሆን ይችላል። ከዚህ ቀደም እንዳልነው ሁሉ፣ አንድን ፋይል ስንደመስስ (ዴሊት ስናደርግ) በፋይሉ ውስጥ የነበረው መረጃ በኮምፒውተራችን ሐርድ ድራይቭ ውስጥ ይቀመጣል፤ ፋይሉን ከሪሳይክል ቢን (Recycle bin) ብናጠፋው እንኳን ወደ ሐርድ ድርራቭ የገባው መረጃ አይጠፋም። ተገቢውን ሶፍትዌር የያዘና ትንሽ እድል ያለው ማንኛውም ሰው ይህንን በድምሰሳ ወደ ሐርድ ድራይቭ የተበተነ ስሱ መረጃችንን በቀላሉ መልሶ ሊያገኘው ይችላል።

የተደመሰሱ (deleted) መረጃዎች በማይገባቸው ሰዎች እጅ እንዳይገቡ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ አለብን፤ መረጃዎቹን እስከወዲያኛው በአስተማማኝ መልኩ የሚያጠፋ ለዚሁ ተብሎ የተሠራ ሶፍትዌር መጠቀም አስፈላጊ ይሆናል። ከእነዚህ ሶፍትዌሮች አንዱ ኢሬዘር (Eraser) ነው፤ በዚህ ምእራፍ በስፋት እንመለከተዋለን። ኢሬዘርን (Eraser) መጠቀም ማለት መረጃ የተጻፈበትን ወረቀት እንደዋዛ “ማንም አውጥቶ አይመለከተውም” በሚል ግዴለሽነት አጨማዶ በቆሻሻ መጣያ ቅርጫት ውስጥ ከመጣል ይልቅ በጥንቃቄ ቆራርጦ እንደመጣል ነው። ስሱ መረጃዎችን ማጥፋት አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ መደምሰስ (ዴሊት ማድረግ) አንዱ አማራጭ ነው። ሆኖም ስለራሳችንም ይሁን ስለድርጅታችን ስሱ መረጃ የያዙ ዴሊት የተደረጉ ፋይሎችን መርምረው ሊያገኙብን ይችላሉ የምንላቸው ሰዎች፣ በተለይም የፖለቲካ ዓላማ ያላቸው ኅይለኛ ቡድኖች ካሉ መረጃዎቹን የያዙ ጊዜ ያለፈባቸውን የመጠባበቂያ ክምችቶች (ባክአፖች) ጭምር በቋሚነት የምናጠፋበትን መንገድ ማሰብ ሊኖርብን ይችላል። አሮጌ/የቆዩ ሐርድ ዌሮችን ማንጻት/ዋይፒንግ (wiping) ሌላው መፍትሔ ሲሆን፣ የከረሙ የኮምፒውተር ተጠቀሚ መስኮቶችን (user accounts) ማጥፋት፣ የኢንተርኔት ሐሰሳ ታሪካችንን (web browsing history) ሲክሊነርን (CCleaner) በመሳሰሉ መሣሪያዎች ማጥፋት አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። ሲክሊነር እና በዚህ ምእራፍ የተጠቀሱ ሌሎችም መሣሪያዎች ኮምፒውተራችንን በተጠቀምን ጊዜ ሁሉ በየቦታው በጊዜያዊነት የተከማቹ ፋይሎችን ሁሉ ፈልገው ሊያጠፉና ሊያጸዱልን ይችላሉ።

አስረጅ ታሪክ

:Snippet

የምእራፉ ዋና ዋና ጭብጦች

 • ስሱ መረጃዎችን ከኮምፒውተራችን እስከመጨረሻው ማስወገድ የሚቻለው እንዴት ነው?
 • ሲዲ እና የመረጃ ማህደር (USB memory sticks) በመሳሰሉ ተንቀሳቃሽ የማከማቻ ማህደሮች ላይ የተጠራቀሙ መረጃዎችን ማስወገድ የሚቻለው እንዴት ነው?
 • በኮምፒውተራችን ላይ ከዚህ ቀደም ምን መረጃ እንደነበረ እንዳይታወቅ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?
 • የተደመሰሱ (ዴሊት የተደረጉ) መረጃዎች መልሰው እንዳይገኙ ኮምፒውተራችንን እንደምን መያዝ ይኖርብናል?

መረጃዎችን መደምሰስ

በቴክኒካዊ አነጋገር በኮምፒውተራችን ላይ “መደምሰስ” (ዴሊት) የሚባል ነገር የለም። አንድን ፋይል ስንደመስስ/ዴሊት ስናደርግ ፋይሉን ከነበረበት ቦታ ወደ ሪሳይክል ቢን (የቆሻሻ ቅርጫት) መውሰዳችን ነው እንጂ እስከመጨረሻው ማጥፋታችን አይደለም ነው። ይህ ማለት የፋይሉ ስም ከኮምፒውተራችን ላይ ይጠፋል። ፋይሉ ቀደሞ የነበረበት ቦታም ባዶ ይሆናል፤ ስለዚህም ይህን የተለቀቀ ቦታ ለሌላ ፋይል ልንጠቀምበት እንችላለን ማለት ነው። ይህ ቦታ በሌላ ፋይል እስኪያዝ ድረስ ግን በተደመሰሰው ፋይል ውስጥ በነበረው መረጃ እንደተያዘ ይቆያል። ነገሩን የፋይል ካቢኔት ምሳሌ ብናየው የበለጠ ግልጽ ይሆናል። በፋይል ካቢኔቱ ውስጥ ብዙ መዝገቦች/ፋይሎች አሉ፤ እያንዳንዱ ፋይልም ስያሜ አለው። በእያንዳንዱ ፋይል ውስጥ ደግሞ የተለያዩ መረጃዎች ይኖራሉ። እንግዲህ፣ አንድን ፋይል ስንደመስስ የፋይሉን ስም ነው የምናጠፋው እንደማለት ነው። የፋይሉ ስም ቢጠፋም፣ በውስጡ የያዘው መረጃ ግን በሌላ እስኪተካ እንዳለ ይቆያል። ዴሊት ስናደርግ (ስንደመስስ) የፋይሉ ስም ከኮምፒውተራችን ስለሚጠፋ በውስጡ የያዘውን መረጃ በቀድሞ ስሙ ፈልገን ልናገኘው አንችልም። በቀላሉ ፈልገን አናግኘው እንጂ ግን በፋይሉ ውስጥ የነበረው መረጃ ሁሉ ተኖ ይጠፋል ማለት አይደለም፤ ልክ እንደ ፋይልካቢኔቱ ሁሉ በሌላ እስኪተካ ይቆያል። ለዚህም ነው ትክክለኛው ሶፍትዌር እስካለን እና ፈጥነን እርምጃ እስከወሰድን ድረስ በስሕተት ያጠፋናቸውን ፋይሎች መልሰን ልናገኛቸው እንችላለን በማለት በምእራፍ 5፡ የጠፉ መረጃዎችን መልሶ ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው? ያወሳነው።

ከዚህም ሌላ፣ ኮምፒውተራችንን በተጠቀምን ቁጥር እኛ ባናውቀውም በርካታ ፋይሎች እንደሚፈጠሩ እና አስተማማኝ ባልሆነ መልኩ እንደሚደመሰሱ መርሳት የለብንም። ለምሳሌ አንድ ሰው ትልቅ ሪፖርት እየጻፈ ነው እንበል። ይህ ሥራ ምናልባት ሳምንት ይፈጅ ይሆናል። የሪፖርቱ ጸሐፊ በየእለቱ ለብዙ ሰዓታት በኮምፒውተሩ ይሠራል። ሰውየው በዚህ ረጅም ሥራው ፋይሉን ሴቭ ባደረገ (ያለው ነገር የፋይሉ አካል እንዲሆነ ባዘዘ) ቁጥር ዊንዶውስ የዶክመንቱን አዲስ ቅጂ ይፈጥራል፤ በሐርድ ድራይቩ ላይም ያጠራቅመዋል። ከቀናት የአርትኦት ሥራ በኋላ እኛ ባናውቀውም ሪፖርቱ በየጊዜው የነበረውን ቅርጽ የሚሳዩ በርካታ አይነቴዎች (versions) ሊኖሩን ይችላል።

ዊንዶውስ በአጠቃላይ የየፋይሎቹን የቆዩ/የቀድሞ አይነቴዎች ይደመስሳል። ነገር ግን ደኅንነትን ለመጠበቅ ሲል በላዩ ላይ ሌላ ነገር (overwrite) ለመጻፍ ብሎ ፋይሉ የነበረበትን የመጀመሪያ ቦታ ሲያስስ አይውልም። ከዚህ ይልቅ የመጨረሻውን የፋይሉን ቅርጽ (አይነቴ / ቨርዥን) ቀደም ሲል ለምሳሌ ባነሳነው የፋይል-ካቢኔት አሠራር የፋይሉን ስም ከአሮጌው ወደ አዲሱ አዙሮ እንደ አዲስ ያስቀምጠዋል። በዚህ አሠራሩም የቀደመውን የፋይሉን አይነቴ ባለበት ይተወዋል፣ ሌሎች ፕሮግራሞች ቦታውን እስኪጠቀሙበት ድረስም ፋይሉ እዚያው ይቆያል። ይህን ዶክመንት ከነዘር ማንዘሩ ማጥፋት እንዳለብን ካመንን የመጨረሻውን አይነቴ መደምሰስ (ዴሊት ማድረግ) በቂ እርምጃ አይሆንም። ዲጂታል መረጃዎቻችን የሚገኙት በኮምፒውተራችን ሐርድ ድራይቭ ላይ ብቻ አለመሆኑንም መዘንጋት አይቻልም። ሲዲዎች፣ ዲቪዲዎች፣ ተንቀሳቃሽ የመረጃ ማህደሮች/ቋቶች፣ ፍሎፒ ዲስኮች፣ ፍላሽ የማስታወሻ ካርዶች፣ ሞባይል ስልኮች፣ ተንቀሳቀሽ ሐርድ ድራይቮች ሁሉ ዲጂታል መረጃዎችን ይይዛሉ። ስለዚህም ስሱ መረጃዎችን ፈጽሞ ለማጥፋት ከተፈለገ በቀጥታ ዴሊት በማድረግ ብቻ ነገሩን መቋጨት እንደማይቻል የተረጋገጠ ነው።

በአስተማማኝ የመደምሰሻ መሣሪያዎች መረጃዎችን ማጽዳት

በዚህ ምእራፍ የተጠቆሙትንም ይሁን መሰል አስተማማኝ የመደምሰሻ (secure deletion) መሣሪያዎች ተጠቀምን ማለት እንደተለመደው “ዴሊት አደርግን” ማለት ብቻ አይደለም፤ የተደመሰሱትን ስሱ መረጃዎች በሌላ ተካናቸው፣ ወይም በላያቸው ላይ ሌላ ነገር ጻፍንባቸው ('overwriting') ማለት ነው። ቀድሞ ባነሳነው የፋይል-ካቢኔት ምሳሌያችን ብንቀጥል፤ የመዝገቦቹ ስሞች ቢቀየሩም በውስጣቸው ያለው መረጃ ግን እንዳለ ባለበት ሊቆይ እንደሚችል ጠቅሰናል። እነዚህ መረጃዎች በእርሳስ እንደተጻፉ እናስብ። አስተማማኝ የማጥፊያ መሣሪያዎችን ተጠቀምን ማለት፣ እነዚህን በእርሳስ የተጻፉ መረጃዎች በላፒስ ማጥፋት ብቻ ሳይሆን፤ ከዚያ በኋላ በጠፋው በእያንዳንዱ ቃል የቀረ ደብዛዛ ምስል ላይ ሌላ ቃል ጻፍንበት እንደማለት ነው። መጀመሪያ በላፒስ አጥፍቶ ከዚያ በላዩ ላይ አዲስ ነገር መጻፍ። በላፒስ የጠፋ ጽሑፍ በደብዛዛውም ቢሆን የመታየት እድል እንዳለው ሁሉ ዴሊት የተደረገ ዲጂታል መረጃም መልሶ ሊገኝና ሊነበብ ይችላል። በዚህ ላይ አዲስ ነገር ተመልሶ ሲጻፍበት ግን የቀድሞው ጽሑፍ የመታየት እድሉ እያነሰ ይሔዳል። ይህ አሠራር ማንጻት/ዋይፒንግ (wiping) ይባላል። በመጀመሪያው ጽሑፍ ላይ ተደጋግሞ በተጻፈበት መጠንም ፈጽሞ ሊታይ/ሊገኝ ወደማይችልበት ደረጃ ይደርሳል፤ የመጀመሪያውን መረጃ ለማንበብ ለሚሞክርም እጅግ አስቸጋሪ ይሆንበታል። የመስኩ ባለሞያዎች በአብዛኛው ሦስት እና ከዚያም በላይ ጊዜ ደራርቦ መጻፍን (overwriting) ይመክራሉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ እንደ መረጃው ስሱነት ለሰባት እና ከዚያም ለሚበልጥ ጊዜ ደራርቦ መጻፍን ያሳስባሉ። የማንጻት/ዋይፒንግ (wiping) ሶፍትዌር በቀጥታ በቂ ሊባል ለሚችል ጊዜ ደጋግሞ አጥፍቶ-የመጻፍ ሥራ ይሠራል፤ ይህ የማይበቃ መስሎ ከታየን ደግሞ የድግግሞሹን መጠን ልንጨምረው እንችላለን።

ፋይሎችን ማንጻት/ዋይፒንግ

ስሱ መረጃዎችን ከሐርድ ድራይቮችም ይሁን ከሌሎች የማከማቻ ማህደሮች/ቋቶች ለማንጻት/ዋይፒንግ (wiping) ሁለት የተለመዱ መንገዶች አሉ። አንድን ነጠላ ፋይል ማንጻት/ዋይፕ (wipe) ይቻላል፤ ወይም በሐርድ ድራይቩ ውስጥ አገልግሎት ላይ ያልዋሉ ቦታዎችን ('unallocated' space) በጅምላ ማንጻት/ዋይፕ (wipe) እንችላለን። በዚህ ላይ ውሳኔ ስንሰጥ አስቀድመን ያነሳነውን የረጅም ሪፖርት ዝግጅት ሒደት ምሳሌያችንን መላልሶ ማስተወስ ይጠቅማል። በሪፖርት ዝግጅቱ መጨረሻ የምናገኘው የሚታይ ፋይል አንድ ብቻ ቢሆንም፣ በዝግጅቱ ሒደት ሴቭ የተደረጉ በሐርድ ድራይቫችን ላይ የተበታተኑ ያለተጨረሱ ቅጂዎች መኖራቸው አይቀርም። አንድን ፋይል ለይተን ብናነጻ/ዋይፕ (wipe) የዚህ ፋይል የመጨረሻ እትም/አይነቴ (ቨርዥን) ፈጽሞ ይጠፋል፤ የተበታተኑት የቀደሙ እትሞቹ/አይነቴዎቹ ግን ባሉበት ይተዋሉ። ለነገሩ እነዚህን በየቦታው የተዘሩ የቀደሙ እትሞቹን ልዩ ሶፍትዌር ካልተጠቀምን በቀር እንኳን ልናነጻቸው ያሉበትንም ቦታ ማግኘት አንችልም። ነገር ግን ባዶ ቦታዎችን (blank space) በጅምላ በማንጻት/ዋይፒንግ (wiping) ከዚህ ቀደም የተደመሰሱ (deleted) መረጃዎች በሙሉ በያሉበት እስከወዲያኛው እንዲነጹ ማድረግ እንችላለን። ይህንን በፋይል-ካቢኔው ምሳሌ ያየነው እንደሆነ ስማቸው ቢጠፋም መረጃዎችን የያዙ ዶክመንቶችን አንድ በአንድ እየፈለጉ መረጃውን እያጠፉ በላዩ ላይ ሌላ መረጃ እንደመጻፍ ነው።

ኢሬዘር (Eraser) በኢንተርኔት በነጻ የሚገኝ፣ ለአጠቃቀም ቀላል የሆነ አስተማማኝ የማጥፊያ/መደምሰሻ መሣሪያ ነው። ኢሬዘርን (Eraser) በመጠቀም ፋይሎችን በሦስት መንገዶች ማንጻት/ዋይፕ (wipe) ይቻላል። አንድ ነጠላ ፋይልን ለይተን ማንጻት፣ በሪሳይክል ቢን (Recycle Bin) የተጠራቀሙትን ፋይሎች አንድ ላይ ማንጻት፣ ወይም በድራይቩ ውስጥ የሚገኙትን አገልግሎት ላይ ያልዋሉ ቦታዎችን (unallocated space) በጅምላ ማንጻት/ዋይፒንግ (wiping) እንችላለን። ኢሬዘር (Eraser) በዊንዶውስ የሚፈጠሩ ስዋፕ ፋይል (swap file) የሚባሉትንም ለማንጻት/ዋይፕ (wipe) ይችላል፤ ዝርዝሩን ወደፊት እናገኘዋለን።

አጠቃቀም! ኢሬዘር - አስተማማኝ የፋይል አወጋገድ መመሪያ (Eraser - Secure File Removal Guide)

አስተማማኝ የመደምሰሻ መሣሪያዎች እኛ ራሳችን ካላዘዝናቸው በቀር የሚታዩ ፋይሎችን የማንጻት/ዋይፕ (wipe) ሥራ አያከናውኑም። ነገር ግን ይህን መሰል መሣሪያዎችን ስንጠቀም ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለብን ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የለብንም። መቼም ስሕተት አያጋጥምም አይባልም፤ ለዚህም ነው ተጠቃሚዎች ሪሳይክል ቢንን (Recycle Bins) እና የመረጃ መልሶ ማግኛ መሣሪያዎችን (data recovery tools) እጅግ ጠቃሚ ሆነው የሚያገኙዋቸው። አንድ ፋይል ዴሊት ባደረግን (በደመሰስን) ቁጥር ወዲያውኑ የማንጻት/ዋይፒንግ (wiping) ልምድ ካለን በስሕተት ያጠፋነውን ፋይል መልሶ ማግኘት የምንችልበትን እድል ሁሉ እያጠበብነው እንሔዳለን። ስለዚህ ብዙ መረጃዎችን ከኮምፒውተራችን ከማንጻታችን/ዋይፒንግ (wiping) በፊት አስተማማኝ የመጠባበቂያ ክምችት መያዛችንን ማረጋገጥ አለብን።

:Snippet

ጊዜያዊ ዳታዎችን ማንጻት

ኢሬዘር (Eraser) በድራይቭ ውስጥ አገልግሎት ላይ ያልዋሉ ቦታዎችን (unallocated space) እየመረጠ ለማንጻት/ዋይፕ (wipe) የሚችልበት አሠራር አስቀድሞ የተደመሰሱ (previously-deleted) ይዘቶችን/መረጃዎችን ብቻ እየመረጠ የሚያነጻ/ዋይፕስ (wipes) በመሆኑ ብዙ የሚየሰጋ አይደለም። የተለመዱ የሚታዩ ፋይሎች አንዳችም የሚሆኑት ነገር የለም፤ አይነኩም። በሌላ በኩል ግን፣ ይህ እውነታ ራሱ ሌላ ቁም ነገር በትኩረት እንድንመለከት ይጋብዘናል፤ ይኸውም ኢሬዘር (Eraser) ያልተደመሰሱ ስሱ መረጃዎችን እንደማያጠፋልን ማወቅ ነው፤ ርቀው የተደበቁ ፋይሎችንም እንዲሁ። ስሱ መረጃዎችን የያዙ ፋይሎች በማይታዩ ፎልደሮች ውስጥ ተቀምጠው ይሆናል፤ ሆን ተብሎ በተሳሳተ ወይም ትርጉም በማይሰጥ የፋይል ስም ተቀምጠውም ሊሆን ይችላል። ይህ ጉዳይ ኤሌክትሮኒክ ዶክመንቶችን በተመለከተ ብዙ የሚያሳስብ አይደለም፤ ነገር ግን ኮምፒውተራችንን እየተጠቀምን እያለ ለምንሰበስባቸው/ለምናገኛቸው (ጊዜያዊ) መረጃዎች ደኅንነት ግን በጣም አስፈላጊ ነው። ለዚህ ጥቂት ምሳሌዎች እንጥቀስ፤

- የኢንተርኔት ማሰሻችን (browser) የሚመዘግባቸው ጊዜያዊ መረጃዎች/ዳታ ይኖራሉ። ይህም የጎበኘናቸውን ድረ ገጾች፣ የተጠቃሚ መግቢያ መረጃዎች (account information)፣ ኦንላይን ቅጾችን ለመሙላት የተጠቀምንባቸውን ግላዊ መረጃዎች፣ በድረ ገጾች ያየናቸውን ምስሎችና ጽሑፎች፣ [*ኩኪስ (cookies)*](/am/glossary#Cookie) ሁሉ ይጨምራል። 

- በኮምፒውተራችን ላይ የምንሠራውን ነገር እንዲቀመጥ ከማዘዛችን (ሴቭ ከማድረጋችን) በፊት ኮምፒውተራችን ሥራ ቢያቆም፣ ይህን ፋይል መልሰን እንድናገኘው የሚረዱን፣ ፋይሉን በጊዜያዊነት የሚያስቀምጡልን አፕሊኬሽኖች አሉ። እነዚህ በጊዜያዊነት የተቀመጡ ፋይሎች ጽሑፎች፣ ምስሎች፣ የሌሎች ፋይሎች ስም፣ ወይም ሌሎች ስሱ መረጃዎችን የያዙ ሊሆኑ ይችላሉ።

- ዊንዶውስ ለተጠቃሚዎቹ ሥራ ለማቅለል ሲል ብዙ ጊዜ የምንጠቀምባቸውን ፋይሎች እና ሊንኮች (መተላለፊያ) ያጠራቅማል፤ ለምሳሌ በቅርቡ የተጠቀምንበትን/የከፈትነውን አፕሊኬሽን አቋራጭ መክፈቻ (shortcuts)፣ የፎልደር መክፈቻ መተላለፊያዎችን (ፎልደሩ ምናልባት እንዲታይ አንፈልግ ይሆናል)፣ እና ሳናነጻ የረሳነውን <b>ሪሳይክል ቢን (Recycle Bin)</b> ሁሉ ዊንዶውስ ያጠራቅመዋል።

- የዊንዶውስ [*ስዋፕ ፋይል (swap file)*](/am/glossary#Swap_file)። የኮምፒውተራችን መረጃ ማጠራቀሚያ (computer's memory) ሲሞላ፣ ለምሳሌ በአሮጌ ኮምፒውተር ብዙ ፕሮግራሞችን በአንድ ጊዜ ስንከፍትበት፣ ዊንዶውስ እየተጠቀምንበት ያለውን መረጃ/ዳታ ቀድቶ ወደ አንድ ትልቅ ፋይል የሚገለብጥበት ጊዜ አለ። ይህ በዚህ አይነቱ ወቅት የሚፈጠረው ትልቅ ፋይል የዊንዶውስ [*ስዋፕ ፋይል(swap file)*](/am/glossary#Swap_file) ይባላል። ይህ ፋይል የተጠቀምንበትን ማንኛውንም መረጃ በሙሉ ይዞ ሊገኝ ይችላል፤ ለምሳሌ ድረ ገጾችን፣ የዶክመንቶቻችንን ይዘት፣ የይለፍ ቃሎችን፣ የኢንክሪፕሽን ቁልፎችን…። ኮምፒውተራችንን ስንዘጋም ቢሆን [*ስዋፕ ፋይል(swap file)*](/am/glossary#Swap_file) አይጠፋም፤ ስለዚህም ራሳችን ማንጻት (wipe) አለብን። 

እነዚህን የመሳሰሉ ጊዜያዊ ፋይሎችን ከኮምፒውተራችን ላይ ጠራርጎ ለማጥፋት ሲክሊነር (CCleaner) የተባለውን በነጻ የሚገኝ መሣሪያ/ሶፍትዌር መጠቀም ይኖርብናል። ሲክሊነር ስሱ መረጃዎችን አጋልጠው ሊሰጡብን የሚችሉትን ኢንተርኔት ኤክስፕሎረር፣ ሞዚላ ፋየርፎክስ (Firefox) እና ማይክሮሶፍት ኦፊስን የመሳሰሉ አፕሊኬሽኖችን እና ዊንዶውስን ራሱን ለማጻዳት ተብሎ የተሠራ ሶፍትዌር ነው። ኮምፒውተራችንን ተጠቅመን በጨረስን ቁጥር ኢሬዘርን (/Eraser) በመጠቀም አገልግሎት ላይ ያልዋሉ ቦታዎችን አድኖ ከማንጻት/ዋይፕ (wipe) ይልቅ ሲክሊነር (CCleaner) ፋይሎችን በአስተማማኝ መንገድ የማጽዳት ብቃት አለው።

አጠቃቀም! ሲክሊነር - አስተማማኝ የፋይል አጠፋፍ እና የጊዜያዊ መረጃዎች አነጻጽ መመሪያ (CCleaner - Secure File Deletion and Work Session Wiping Guide)

አስተማማኝ የመደምሰሻ መሣሪያዎችን መጠቀም፤ ቀላል ዘዴዎች!

እስከ አሁን ስሱ መረጃዎችን እየተከታተልን የምናጠፋ (ኢሬዝ) ቢሆንም እንኳን በኮምፒውተራችን እና በመረጃ ማጠራቀሚያ መዝገቦች ላይ የሚገኙ መረጃዎቻችን ወጥተው ሊታዩ የሚችሉባቸውን ጥቂት መንገዶች አይተናል። እነዚህን መረጃዎች በቋሚነት ለማንጻት/ዋይፕ(wipe) ልንጠቀምባቸው የምንችላቸውን መሣሪያዎችም አውቀናል። እነዚህን መረጃዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ለሚጠቀሙም ሆነ ለበካሮቹ፣ ጥቂት ቀላል የአጠቃቀም ምክሮችን እዚህ ላይ ማስታወስ እንችላልን፤ እነዚህ ነጥቦች ድራይቮቻችንን በአስተማማኝ እና በፍጥነት ለማጽዳት ይጠቅሙናል።

የሚከተሉትን ነገሮች ቋሚ ልምዶቻችን እንዲሆኑ ብናደርግ የምናገኘው ጥቅም እጅግ የበዛ ነው፤

 • ጊዜያዊ ፋይሎችን በሲክሊነር (CCleaner) በቋሚነት በየተወሰነ ጊዜው ማንጻት/ዋይፕ(wipe)

 • ስሱ ኤሌክትሮኒክ ዶክመንቶችን በዊንዶውስ መደምሰሻ (ዴሊት) ወይም ወደ ሪሳይክል ቢንን (Recycle Bin) በማስገባት ለማጥፋት ከመሞከር ይልቅ ከነጭራሹ ማንጻት/ዋይፕ(wiping)

 • ኢሬዘርን (Eraser) በመጠቀም የዊንዶውስን ስዋፕ ፋይል (swapfile) በቋሚነት በየጊዜው ማንጻት/ዋይፕ(wipe)

 • በሐርድ ድራይቮች፣ የመረጃ ቋቶች እና በሌሎች የማከማቻ መዝገቦች የሚገኙ፣ በቅርቡ የተደመሰሱ መረጃዎችን ሊይዙ የሚችሉ ባዶ ቦታዎችን በኢሬዘር (Eraser) በቋሚነት በየጊዜው ማንጻት/ዋይፕ(wipe) ። ፍሎፒ ዲስኮች፣ መላልሶ ሊጻፍባቸው የሚችሉ ሲዲዎችና ዲቪዲዎች፣ (የካሜራ፣ የተንቀሳቃሽ የሙዚቃ ማጫወቻዎች እና የሞባይል ስልኮች) ተነቃይ ፍላሽ ሜሞሪ ካርዶች ሁሉ እዚህ ውስጥ የሚካተቱ ናቸው።

የማከማቻ ማህደርን ሙሉ በሙሉ ማንጻት፤ ቀላል ዘዴዎች!

አንድን የመረጃ ማከማቻ ማህደር/ቋት (storage device) ሙሉ በሙሉ ማንጻት/ዋይፕ (wipe) ያስፈልገን ይሆናል። ኮምፒውተራችንን ለሌሎች ሰዎች በስጦታ ስንሰጥ ወይም ስንሸጠው ሐርድ ድራይቩን አውጥቶ ማስቀረት የሚመከር ነው፤ ገዢው አዲስ ሐርድ ድራይቭ ገዝቶ መጠቀም ይችላል። ይህን ማድረግ ካልተቻለ ግን ኮምፒውተሩን ከመስጠታችን በፊት ሐርድ ድራይቩን በኢሬዘር (Eraser) ማንጻት/ዋይፕ(wipe) ግዴታ ነው። ሐርድ ድራይቩን ለማስቀረት ብንችልም አንድ ቀን በውስጡ ያለውን ነገር ሁሉ ማንጻት/ዋይፕ(wipe) እንፈልግ ይሆናል። አዲስ ኮምፒውተር ስንገዛም የሚሆነው ይኸው ነው፤ መረጃዎቻችንን ከአሮጌው ወደ አዲሱ ከገለበጥን በኋላ በአሮጌውን ማንጻት/ዋይፕ(wipe) ይኖርብናል። ኮምፒውተሩን ለመጣል ብንወስንም የሚሆነው በአብዛኛው ተመሳሳይ ነው፤ እዚህ ላይ ግን ኮምፒውተሩን መሰባበር አለብን። (ብዙዎቹ ባለሞያዎች በአንድ ወቅት ስሱ መረጃ ይዞ የነበረ የማከማቻ ማህደርን ከመጣላችን በፊት ቢቻል በመዶሻ ብጤ አጥብቆ መሰባበርን ይመክራሉ፤ ይህ ኮምፒውተርንም ይጨምራል።)

አሁን ከጠቀስናቸው ሁኔታዎች በአንዱ ምክንያት ሐርድ ድራይቩን በኢሬዘር (Eraser) ሙሉ በሙሉ ማንጻት/ዋይፕ(wipe) ሊኖርብን ይችላል። ሆኖም የኦፐሬቲንግ ሲስተሙ በድራይቩ ላይ እስካለ ድረስ እስካለ ድረስ ይህን ማድረግ አይቻልም። ይህን ለማድረግ ቀላሉ ዘዴ ድራይቩን ከኮምፒውተሩ ለይቶ በውጫዊ የዩኤስቢ ድራይቭ ማቀፊያ (external USB 'drive enclosure') ውስጥ መክተት፣ ከዚያም ኢሬዘር (Eraser) ከተጫነበት ሌላ ኮምፒውተር ጋራ ማያያዝ ነው። ከዚያ በውጫዊው ድራይቭ ውስጥ ያሉትን መረጃዎች በሙሉ መጀመሪያ መደምሰስ (ዴሊት ማድረግ)፣ ከዚያ ደግሞ በኢሬዘር (Eraser) ያልተያዙ ቦታዎቹን (unallocated space) በሙሉ ማንጻት/ዋይፕ(wipe) ይቻላል። ደግነቱ ይህን የምናደርገው እጅግ አልፎ አልፎ ነው።

መላልሶ በሚጻፍበት ሲዲ ወይም ዲቪዲ ላይ የተጻፈን መረጃ/ዳታ ለማንጻት/ዋይፕ(wipe) ከመሞከር ይልቅ ሲዲውን ራሱን ሰባብሮ መጣል ይመረጣል። አስፈላጊ ከሆነ ማስቀረት የምንፈልገውን መረጃ በአዲስ ሲዲ/ዲቪዲ ላይ መጻፍ እንችላለን። እርግጥ መልሶ መጻፍን የማይፈቅዱ ሲዲዎች ሲሆኑ መጀመሪያውኑም ከመሰባበር ሌላ ምርጫ አይኖረንም። በሲዲ እና ዲቪዲ ላይ የተጻፉ መረጃዎችን ፈጽሞ ማጥፋት እጅግ አስገራሚ በሆነ መልኩ አስቸጋሪ ነው። ተሰባብረው ከተጣሉ ሲዲዎች መረጃ ለማግኘት መቻሉን ሰምተን ይሆናል። እነዚህ ታሪኮች እውነት ቢሆኑም ከተሰባበሩ ሲዲዎች መረጃዎችን ሰብስቦ፣ ትርጉም በሚሰጥ መንገድ እንደገና ማዋቀር ከፍተኛ እውቀትን እና ጊዜን የሚፈልግ ሥራ ነው። ስለዚህ ሲዲዎቹን ሰባብርን ስንጥል በውስጣቸው ያለውን መረጃ ለማግኘት የሚፈልገው ሰው፣ ይህን አስቸጋሪ መንገድ አልፎ የማግኘት ሙከራ የማድረግ አቅም እና ፍላጎት ይኖረው እንደሆነ መመዘን አለብን። ሲዲዎቹን መቆራረጥና መሰባበር ብዙ የሚያስቸግር አይደለም። ባይሆን ስብርባሪዎቹን/ቁርጥራጮቹን ከመኖሪያ ቤታችን እና ከሥራ ቦታችን በራቁ የተለያዩ ቦታዎች ለያይቶ መጣል ነው።

:Snippet

ተጨማሪ ንባብ