1. ኮምፒውተርን ከማልዌር እና ከሰርጎ ገቦች (hackers) እንዴት መከላከል ይቻላል?

Updated2010

መመሪያው በወቅቱ አልተሻሻለም፤ በቅርቡ ይሰረዛል

የኮምፒውተራችን ጤንነት የኢንተርኔት ደኅነታችንን የማረጋገጥ የመጀመሪያ እርምጃ ነው። ስለዚህም ስለጠንካራ ምሥጢራዊ የይለፍ ቃል (password)፣ ምሥጢራዊነቱ ስለተጠበቀ ግንኙነት፣ ስለአስተማማኝ የፋይል አጠፋፍ እና ስለመሳሉት ከመጨነቃችን በፊት ኮምፒውተራችን ጤናው የተጠበቀ መሆኑን ማረጋገጥ አለብን። ለምሳሌ ያህል ኮምፒውተራችን ለሰርጎ ገቦች (hackers) አለመጋለጡን፣ ማልዌር (malware) በመባል በሚታወቁት ቫይረሶች አለመጠቃትን፣ የስለላ መረቦች (spyware)ን በመሳሰሉ ጎጂ ሶፍትዌሮች አለመወረሩን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው። አለበለዚያ የኢንተርኔት ደኅነታችንን ለመጠበቅ የምንወስዳቸው ሌሎች የጥንቃቄ እርምጃዎች ሁሉ አስተማማኝ ለውጥ ላያመጡ ይችላሉ። ዘራፊው እቃ ቤት ውስጥ እያለ የቤቱን መግቢያ በር መተው፣ ከዚያ ደግሞ ዋናውን የመውጫ በር ክፍት አድርጎ ሌባውን እንደመፈለግ ይሆንብናል።

ይህ ምእራፍ ሶፍትዌሮቻችንን እንዴት ማሻሻል እንዳለብን፣ ኮምፒውተሮችቻን ቁጥራቸውና አይነታቸው እየበዛ በመጡት ማልዌር (malware) እንዳይወረር፣ በሰርጎ ገቦች (hackers) እንዳይጠቃ ለመከላከል የሚያስችሉንን መሳሪያዎች ያስተዋውቀናል። ከመሣሪያዎቹ መካከልም አቫስት (Avast)ስፓይቡት (Spybot) እና ኮሞዶ ፋየርዎል (Comodo Firewall) ይገኙበታል። ለእነዚህ ጥቃቶች በብዛት የተጋለጠው ዊንዶስ (Windows) የተባለው ኦፕሬቲንግ ሲስተም በመሆኑ በዚህ ምእራፍ የተጠቀሱት መሣሪያዎች (tools) ለዚሁ የተስማሙ ናቸው። ሆኖም የጂኤንዩ/ሊኑክስ (GNU/Linux) እና አፕል ኦኤስኤክስ (Apple OS X) ተጠቃሚዎችም ለአደጋው ሊጋለጡ እንደሚችሉ በመረዳት እዚህ የተዘረዘሩትን የጥንቃቄ እርምጃዎች መከተል አለባቸው።

###አስረጅ አጋጣሚ###

:Snippet

የምእራፉ ዋና ዋና ጭብጦች

 • ማልዌር (malware) በመረጃችን ምሥጢራዊነት እና ደኅንነት፣ በኮምፒውተራችን ጤንነት እና በሌሎች የደኅንነት መጠበቂያ መሣሪያዎች/ዘዴዎች ላይ የሚያስከትለው አደጋ ምንድን ነው?
 • ራሳችንን ከአደጋ ለመጠበቅ እንችል ዘንድ እንድንጠቀምባቸው የምንመከራቸውን መሣሪያዎች/ዘዴዎች እንዴት መተግበር እንችላለን?
 • ሶፍትዌሮችን በየጊዜው በማደስ (update) እንዴት የኮምፒውተራችንን ደኅንነት መጠበቅ እንችላለን?
 • ለሽያጭ ከሚቀርቡት ይልቅ ነጻ ሶፍትዌሮችን/ፍሪዌር (freeware) መጠቀም ያለብን ለምንድን ነው? ለሽያጭ የሚዘጋጁት የመገልገያ ጊዜያቸው ካለፈ፣ ወይም እውነተኛ ያልሆነና ተመሳስሎ የተሰራ ሐሰተኛ ሶፍትዌር ገዝተን የምንጠቀም ከሆነ ሊያጋጥም የሚችለውን አደጋ ለመቀነስ ነጻ ሶፍትዌሮችን፣ የሚቻል ከሆነ ደግሞ ዝነኞቹን የኤፍኦኤስኤስ (FOSS) መሣሪያዎች መጠቀም ይመረጣል።

ቫይረስ

ቫይረሶችን በተለያየ መንገድ መከፋፈል ይቻላል። እያንዳንዱ የመከፋፈያ ዘዴ የየራሱ ስያሜና ንኡስ ክፍሎች አሉት። በጣም የሚታወቁትም ዎርሞች፣ ማይክሮ ቫይረሶች፣ ትሮጃኖች፣ ባክዶሮች ናቸው። አብዛኞቹ እነዚህ ቫይረሶች በኢንተርኔት ውስጥ በኢሜይል፣ በበካይ ድረ ገጾች ወይም አስተማማኝ ጥበቃ የማይደረግላቸውን ኮምፒውተሮች ለማጥቃት በሚዘጋጁ ሌሎች መንገዶች ይሰራጫሉ። ሌሎቹ ቫይረሶች ደግሞ ዩኤስቢ የማስታወሻ ቋት እና ተገንጣይ የማስታወሻ ማህደርን (external hard drives) በመሳሰሉ ተንቀሳቃሽ የመረጃ ቋቶች ይተላለፋሉ። እነዚህ የመረጃ ቋቶች ያገኘ ሰው በውስጣቸው ያለውን መረጃ ለማግኘት እና ተጨማሪ ነገሮችን ለመጨመርም ይችላል። ይህም ለቫይረሶች መሰራጨት መንገድ ይከፍታል። ቫይረሶች በኮምፒውተራችን ውስጥ ያለንን መረጃ እና ፋይል ሊበክሉ፣ ሊያዛቡ እና ጨርሶ ሊያጠፉም ይችላሉ። በተገንጣይ የማስታወሻ ማህደር የሚገኝ መረጃም በቫይረሶች ተመሳሳይ ጉዳት ሊደርስበት ይችላል። ከዚህም አልፎ ቫይረሶች ኮምፒውተራችንን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረው ሌሎች ኮምፒውተሮችን ለማጥቃት ጭምር እንደመሣሪያ ሊጠቀሙበት ይችላሉ። ደግነቱ ራሳችንንም ሆነ መረጃ የምንለዋወጣቸውን ሰዎች ከእነዚህ አደገኛ ቫይረሶች የምንከላከልባቸው በርካታ ጸረ ቫይረስ መሣሪያዎች አሉ።

ጸረ ቫይረስ ሶፍትዌር###

ለዊንዶስ ተጠቃሚዎች አቫስት (Avast) የተባለ እጅግ ጠቃሚ *ፍሪዌር/ነጻ(freeware) ጸረ ቫይረስ ፕሮግራም አለ። አቫስት ለአጠቃቀም ቀላል፣ በየጊዜው ራሱን የሚያድስ፣ በነጻ የሚገኝ እና በጸረ ቫይረስ ባለሞያዎችም የተመሰከረለት ፕሮግራም ነው። የአቫስት (Avast) ተጠቃሚ ለመሆን የሚጠይቀው በ14 ወር አንድ ጊዜ ለአገልግሎቱ በነጻ መመዝገብ ብቻ ነው፤ ፕሮግራሙም ይሁን በየጊዜው ማደሱ ሁሉ በነጻ የሚገኝ አገልግሎት ነው።

አጠቃቀም! (የአቫስት አጠቃቀም መመሪያ)Avast! - Anti-Virus Guide

ክሌም ዊን (Clam Win) የአቫስት እና የሌሎች በርካታ ታዋቂ በሽያጭ የሚገኙ ጸረ ቫይረስ ፕሮግራም የኤፍኦኤስኤስ(FOSS) አማራጭ ነው። ክሌም ዊን የማያሟላቸው የጥሩ ጸረ ቫይረስ ፕሮግራም ባህርያት ቢኖሩም፤ ሶፍትዌሮችን እንድንጭን በማይፈቅዱልን ኮምፒውተሮች ላይ ስንጠቀም የሚገጥመንን አደጋ ይቀንሳል፤ ክሌም ዊንን በዩኤስቢ ሜሞሬ ስቲክ በመያዝ ኮምፒውተሩን መፈተሽ (scan) እንችላለን። ምሥጢራዊነትን የሚፈልጉ መረጃዎችን የግድ በኢንተርኔት ካፌ ወይም በመሰል የሕዝብ መገልገያዎች በሚገኙ ኮምፒውተሮች እንድንጠቀም የሚያስገድድ ሁኔታ ሲገጥመን ክሌም ዊንን እጅግ ጠቃሚ መፍትሄ ነው።

አስተማማኝ የጸረ ቫይረስ ሶፍትዌር አጠቃቀም

 • ሁለት (ወይም ከዚያ በላይ) ጸረ ቫይረስ ፕሮግራሞችን በአንድ ጊዜ መጠቀም የለብንም። ሁለት ጸረ ቫይረሶችን በአንድ ላይ መጠቀም ኮምፒውተራችንን ከሚገባው በላይ ፍጥነቱን በመቀነስ መሥራት እንዲያቆም ሊያደርገው ይችላል። ስለዚህ አንዱን ጸረ ቫይረስ ከመጫናችን በፊት ከዚያ በፊት የነበሩትን ከኮምፒውተራችን የፕሮግራሞች ዝርዝር ማስወገድ ወይም ኢ-መጫን (Uninstall) ያስፈልጋል።

 • የምንጠቀምበት ጸረ ቫይረስ ፕሮግራም ወቅታዊ ማደሻዎች/ማሻሻያዎችን (Updates) እንደሚያደርግና እንደሚፈቅድ ማረጋገጥ አለብን። ብዙውን ጊዜ በአዳዲስ ኮምፒውተሮች ላይ ተጭነው የሚመጡ ለሽያጭ የሚዘጋጁ ጸረ ቫይረሶች መመዝገብን (registered) እና መክፈልን የሚጠይቁ ናቸው፤ ከሆነ ወቅት በኋላም ማደሻዎችን/ማሻሻያዎችን ማግኘት ያቆማሉ። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ እንድንጠቀምባቸው የተጠቀሱት ሶፍትዌሮች በሙሉ በየጊዜው ማሻሻዎችን በነጻ የሚሰጡ ናቸው።

 • ጸረ ቫይረሳችን በየጊዜው ራሱን እያሻሻለ መሆኑን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው። አዳዲስ ቫይረሶች በየእለቱ ይፈጠራሉ (ይጻፋሉ)፣ ይሰራጫሉ። ለእነዚህ አዳዲስ ቫይረሶች የተዘጋጀውን ማርከሻ በወቅቱ እያገኘን ጸረ ቫይረስ ፕሮግራማችን ካልተሻሻለ ኮምፒውተራችን ለአደጋ የተጋለጠ ይሆናል። አቫስት (Avast) የኢንተርኔት ኮኔክሽን ሲኖረን በራሱ ማሻሻያዎችን ፈልጎ ያገኛል።

 • ጸረ ቫይረስ ፕሮግራማችን ቫይረሶችን “ዘወትር በተጠንቀቅ“ እንዲያድን መፍቀድ ('always on') እጅግ አስፈላጊ ነው። የተለያዩ ዘዴዎች ይህንን የሚፈቅዱበት የተለያየ አጠቃቀምና ስያሜ አላቸው። አንዱ “ሪልታይም ፕሮቴክሽን” ('Realtime Protection') ሲለው በሌላው ፕሮግራም ደግሞ “ሬዚደንት ፕሮቴክሽን” ('Resident Protection,') የሚል ስያሜ ሊሰጠው ይችላል። የአቫስት መመሪያ (Avast Guide)ክፍል3.2.1 ስለ“ሬዚደንት ስካነር” ('Resident Scanner') ዝርዝር መረጃ ይሰጣል።

 • በኮምፒውተራችን ውስጥ የሚገኙ ፋይሎችን በየጊዜው በቋሚነት በጸረ ቫይረስ መፈተሽ (Scan) በጣም አስፈላጊ ነው። ይህ ማለት በየዕለቱ ፍተሻ ማድረግ አለብን ማለት ላይሆን ይችላል። በተለይም ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ጸረ ቫይረሳችን “ዘወትር በተጠንቀቅ” ('always on') ከሆነ በየዕለቱ ፍተሻ (Scan) ማድረግ አያስፈልገንም። በምን ያህል ጊዜ ልዩነት ፍተሻ ማድረግ እንዳለብን የሚወስኑ ሌሎች ሁኔታዎች ይኖራሉ። በቅርቡ በማያውቁት (የራስዎ ባልሆነ) ኔትወርክ/መረብ ወደ ኢንተርኔት በመግባት ግንኙነት አድርገዋል? የመረጃ ማህደሮችን (USB memory sticks) የተዋዋሱት/የተለዋወጡት ከእነማን ጋራ ነው? እንግዳ እና አጠራጣሪ የሆኑ መልእክቶችንና አባሪዎችን (attachments) በኢሜል ይደርሱዎታል? በቤትዎ ወይም በሥራ ቦታዎ በቅርቡ ከቫይረስ ጋራ የተያያዘ ችግር የገጠመው ሰው አለ? ፋይሎችን ስለመፈተሽ የበለጠ መረጃ ለማግኘት የአቫስት መመሪያ (Avast Guide) መመልከት!

የቫይረስ ጥቃትን መከላከል

 • በኢሜይል የሚላኩ አባሪዎችን (attachments) ሲከፍቱ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያድርጉ። ከማያውቁት ላኪ/ምንጭ በኢሜይል አባሪነት የተላከ ፋይል ፈጽሞ አለመክፈት የተመረጠ ነው። አባሪውን መክፈት የግድ የሚያስፈልግ ከሆነ፣ በቅድሚያ አባሪውን ወደኮሚፒውተርዎ ይውሰዱ/ያውርዱ (ሴቭ ያድርጉት)፤ ከዚያ አባሪውን ለመክፈት የሚችለውን አፕሊኬሽን (ማይክሮሶፍት ወርድ፣ አዶቤ አክሮባት ወዘተ) ይክፈቱ። ፋይሉን በደብል ክሊክ (double-clicking) ወይም በኢሜይል ፕሮግራሙ በቀጥታ (automatically) እንዲከፈት ከማድረግ ይልቅ በፕሮግራሙ ፋይል በኩል በራስ (manually) መክፈት በቫይረስ የመጠቃት እድልን ይቀንሳል።

 • ተንቀሳቃሽ የመረጃ ቋቶችን (ሲዲ፣ ዲቪዲ፣ የማስታወሻ ማህደር- memory sticks) ከኮምፒውተሮቻችን ጋራ ከማገናኘታችን በፊት ሒደቱ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል መገመት አለብን። ስለዚህ በቅድሚያ የጸረ ቫይረስ ቅጂያችን ወቅታዊ (latest) መሆኑን፣ መፈተሻውም (scanner) በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ማረጋገጥ እጅግ አስፈላጊ ነው። በኦፐሬቲንግ ሲስተማችን ውስጥ “በቀጥታ አጫውት” (AutoPlay) የሚል ማዘዣን ማስቆምም መልካም ሐሳብ ነው። ቫይረሶች ይህን ማዘዣ ኮምፒውተሩን ለመበከል ሊጠቀሙበት ይችላሉ። ዊንዶስ ኤክስፒ የሚጠቀሙ የሚከተለውን ሒደት በመከተል ይህን ማድረግ ይችላሉ። ወደ ማይ ኮምፒውትር (My Computer) መሄድ፤ በመረጃ ቋቱ (ሲዲ፣ ዲቪዲ፣ የማስታወሻ ማህደር/memory sticks) ላይ ቀኝ-ንክን (right-clicking) መጫን፤ ፕሮፐርቲስን (Properties) መምረጥና ቀጥታ አጫውትን (AutoPlay) መጫን። ለእያንዳንዱ የይዘት አይነት እርምጃ አትውስድ (Take no action) ወይም “እርምጃ እንድመርጥ ቀድመህ አሳውቀኝ” (Prompt me each time to choose an action) የሚለውን መርጦ “ይሁን” (OK) የሚለውን መጫን።

 • በተጨማሪም ለሽያጭ ከሚቀርቡት ይልቅ በነጻ ለሁሉም የሚቀርቡትን ሶፍትዌሮች (open source software) በመጠቀም የተወሰኑትን ቫይረሶች መከላከል ይቻላል። እነዚህ በነጻ ለሁሉም የሚቀርቡት ሶፍትዌሮች የበለጠ አስተማማኝ ናቸው፤ ቫይረስ ፈጣሪዎችም በአብዛኛው እነዚህን ሶፍትዌሮች ኢላማ አያደርጓቸውም።

:Snippet

ስፓይዌር

ስፓይዌር በኮምፒውተራችን ላይ እና በኢንተርኔት ምን እየሠራን እንደሆነ የሚያሳየውን መረጃ ሰብስቦ ይህን ማወቅ ለሌለባቸው አካላት የሚያደርስ ሶፍትዌር ነው። ይህ ፕሮግራም በመተየቢያ ገበታ (keyboard) የጻፍናቸውን ቃላት፣ የማውሳችንን (mouse) እንቅስቃሴ፣ የጎበኘናቸውን ድረ ገጾች እና ሌሎችንም ዝርዝሮች መመዝገብ ለሦስተኛ ወገን ማስተላለፍ ይችላል። ይህ ቫይረስ የኮምፒውተራችንን ደኅንነት አደጋ ውስጥ የሚከት ሲሆን፤ ምሥጢራዊ መረጃዎቻችንን፣ የምንገናኛቸውን ሰዎች ማንነት እና የምናደርገውን እንቅስቃሴ ሁሉ ለሌሎች ወገኖች ይፋ የሚያደርግ ጭምር ነው።

ኮምፒውተሮች በስፓይዌር የሚጠቁበት መንገድ ለቫይረስ ከሚጋለጡበት በእጅጉ የተቀራረበ ነው፤ ስለዚህም ቀደም ሲል ቫይረሶችን ስለመከላከል የተጠቀሰው በሙሉ ሁለተኛ ደረጃ ማልዌር ስፓይዌሮች ለመቋቋምም ይጠቅማል። የስፓይዌር ዋና ምንጮች ጤናማ ያልሆኑ ድረ ገጾች በመሆናቸው ለምንጎበኛቸው/ለምንከፍታቸው ድረ ገጾች ከፍተኛ ትኩረት መስጠት አለብን። የድረ ገጽ መፈለጊያችን (browser) የደኅንነት መጠበቂያዎችም በሚገባ ማስተካከል ይኖርባቸዋል።

:Snippet

ጸረ ስፓይዌር ሶፍትዌር

ቀደም ሲል ካነሳነው አደጋ ኮምፒውተሮችን ለመጠበቅ ጸረ ስፓይዌር መሣሪያዎችን መጠቀም እንችላለን። ከእነዚህ የመከላከያ ፕሮግራሞች መካከል አንዱ ስፓይቦት (Spybot) ነው። ስፓይቦት ጸረ ቫይረስ ፕሮግራሞች የማይደርሱባቸውን ወይም የሚያልፏቸውን ማልዌሮች (malware) ካሉበት ፈልጎ ያገኛቸዋል፣ ያጠፋቸዋልም። ልክ እንደ ጸረ ቫይረስ ስፓይቦት (Spybot) ማሻሻያ በየጊዜው መጫን እና ፍተሻ (scan) ማካሄድ እጅግ አስፈላጊ ነው።

አጠቃቀም! ስፓይቦት - የጸረ ስፓይዌር መመሪያ (Spybot: Anti-Spyware Guide)

የስፓይዌር ወረራን መከላከል

 • ድረ ገጾችን ስንጎበኝ በንቃት መመልከት የሚገቡን ነገሮች አሉ። በራሳቸው በቀጥታ (automatically) የሚከፈቱ (ብቅ የሚሉ) የመፈለጊያ መስኮቶች (browser windows) ሲያጋጥሙን በቸልተንነት “ቀጥል” ወይም “አዎ” (Yes or OK) ከማለት ይልቅ በቅድሚያ በጥንቃቄ ማንበብ አለብን። ጥርጣሬ የሚያሳድር ነገር ሲገጥመን “ፖፕ አፕ ዊንዶውስ”ን (pop up windows) በመስኮቱ የቀኝ ጫፍ ላይ የሚገኘውን የመዝጊያ ምልክት “X” በመጠቀም መዝጋት ይገባል፤ መስኮቱን “የለም/ሰርዝ” (Cancel) ከሚለው ይልቅ በ“X” መዝጋት ይመከራል። ይህ የመዝጊያ መንገድ (“X”) ሊያታልሉን/ሊያሳስቱን የሚፈልጉ ድረ ገጾች ማልዌሮችን (malwares) በኮምፒውተራችን ላይ እንዳይጨኑ ይረዳናል።

 • የድረ ገጽ መፈለጊያችንን (Web browser) የደኅንነት ጥበቃ ማሻሻል ሌላው እርምጃ ነው። ለዚህም መፈለጊያችን በምንጎበኛቸው ድረ ገጾች ውስጥ ሊደበቁ የሚችሉ አደገኛ ፕሮግራሞችን ያለእኛ ፈቃድ በቀጥታ እንዳይከፍት ማድረግ ይቻላል። የምንጠቀመው ሞዚላ ፋየርፎክስ (Firefox) ከሆነ ኖስክሪፕት (NoScript ) የተባለውን ተጨማሪ አገልግሎች መጫን እንችላለን። ዝርዝሩ *በፋየርፎክስ መመሪያ (Firefox Guide) * ክፍል አራት (Section 4) ይገኛል።

 • እንዲህ አይነት ነገሮች ከማናውቃቸው ወይም ከማናምናቸው ድረ ገጾች ከመጡልን ፈጽሞ መክፈት የለብንም።

:Snippet

ፋየርዎል

ፋየርዎል በኢንተርኔት አማካኝነት ወደኮምፒውተራችን የሚመጣን ዳታ/መረጃ በመጀመሪያ የሚያይ ፕሮግራም ነው። የምንልከው መረጃ ከመሄዱ በፊት ለመጨረሻ ጊዜ የሚገኛነውም ከፋየርዎል ጋራ ነው። ፋየርዎል በአንድ ቤት በር ላይ እንደቆመ የጥበቃ ሠራተኛ ሊታይ ይችላል። የሚመጡትን መረጃዎች ይቀበላል፣ ይመረምራል፤ ወጪና መጪ ዳታዎችን በተመለከተም ውሳኔ ይሰጣል። በመሠረቱ ቫይረሶች እና ሰርጎ ገቦች (hackers) ኮምፒውተራችንን እንዲያገኙ መንገድ ከሚከፍቱ የማይታመኑ የኢንተርኔት እና የአካባቢ መረቦች (local networks) መጠንቀቅ እጅግ አስፈላጊ ነው። የዚያኑ ያህልም ከእኛ ኮምፒውተር የሚወጡትን/የሚላኩትንም መከታተል አስፈላጊ መሆኑን መዘንጋት የለብንም።

ጥሩ ፋየርዎል በኮምፒውተራችን ላይ የሚገኝ ማንኛውም ፕሮግራም ሥራ ከመጀመሩ በፊት ፈቃዳችንን እንዲያገኝ ግድ ይለዋል። ከፕሮግራሞቻችን አንዱ በኢንተርኔት የውጭውን ዓለም ለመገናኘት ቢሞክር፣ ፋየርዎላችን ያግደዋል፤ ከዚያ ቀድም ፈቃድ የተሰጠው ፕሮግራም ካልሆነም ስለሙከራው ለእኛ ያሳውቀናል። ይህን የሚያደርገው በዋናነት በእኛ ኮምፒውተር የሚገኝ ማልዌር ወደሌሎች እንዳይሰራጭ ወይም ሰርጎ ገቦችን ወደ እኛ እንዳይጋብዝብን ነው። በመሆኑም ፋየርዎል ኮምፒውተራችን ለአደጋ ሲጋለጥ የቅድመ ማስጠንቀቂያ በመስጠት እና የሁለተኛ ደረጃ መከላከያ ደጀን በመሆን ያገለግላል።

ፋየርዎል ሶፍትዌር

በቅርብ ለተጠቃሚዎች እየደረሱ የሚገኙ የማይክሮሶፍት ዊንዶውስ ፕሮግራሞች በቀጥታ በራሱ ሥራ የሚጀምር አስቀድሞ የተገጠመ ፋየርዎል አላቸው። አሳዛኙ ነገር የዊንዶውስ ፋየርዎል በብዙ መልኩ ውሱንነቶች ያሉበት መሆኑ ነው። በተለይ የሚላኩ/ወጪ ግንኙነቶችን የማይፈትሽ መሆኑ ተጠቃሽ ነው። ለመጠቀም ከበድ ያለ መሆኑም ሌላ ችግር ነው። ሆኖም ኮምፒውተራችንን በተሻለ መንገድ መጠበቅ የሚችል ኮሞዶ ፋየርዎል (Comodo Firewall) የተባለ ነጻ (freeware) ፕሮግራም አለ።

አጠቃቀም! የኮሞዶ ፋየርዎል መመሪያ (Comodo Firewall Guide)

የማያስተማምኑ የግንኙነት መረቦችን (network connections) መከላከል

 • ጥበቃ የሚያስፈልጋቸውን ስሱ ሥራዎች በምናከናውንበት ኮምፒውተር ላይ ለሥራችን አስፈላጊ የሆኑ ፕሮግራሞችን ብቻ መጫን አለብን። እነዚህን ፕሮግራሞች ከተመሰከረላቸው ምንጮች ማግኘታችንን ማረጋገጥ ይኖርብናል። የማንጠቀምባቸውን ሶፍትዌሮች ማስወገድ (ኢጫን) ጠቃሚ ነው።

 • የማንጠቀምበት ጊዜ ሁሉ ኮምፒውተራችንን ከኢንተርኔት መስመር ግንኙነትን ማለያየት (Disconnect)፣ ወደ መኝታ ስንሄድም ኮምፒውተሩን ሙሉ በሙሉ ማጥፋት ይኖርብናል።

 • የዊንዶውስ መክፈቻ የምሥጢር/የይለፍ ቃላችንን/ቁልፋችንን ለማንም ቢሆን አሳልፎ መስጠት አይገባም።

 • የማንገለገልባቸው፣ ነገር ግን በሥራ ላይ (enable) የሚገኙ “የዊንዶውስ አገልግሎቶች” ('Windows services') ካሉ ማስቆም (disable) አለብን። ለዝርዝር መረጃ ተጨማሪ ንባብ የሚለውን ክፍል ይመልከቱ።

 • በቢሯችን የሚገኘው የግንኙነት መረብ የመከላከያ ፋየረዎል ከሌለው አሁኑኑ መጫን ይገባል። ገበያ ላይ በሽያጭ የሚገኙ ብሮድባንድ ጌትዌይስ (gateways) ለአጠቃቀም ቀላል ናቸው፤ የግንኙነት መረባችንንም በተሻለ መንገድ ይጠብቃሉ። ይህንን ወደተግባር ለመቀየር ከየት መጀመር እንዳለብን እርግጠኛ ካልሆንን የቢሯችንን የግንኙነት መረብ የዘረጉትን ባለሞያዎች በማነጋገር መጀመር እንችላለን።

:Snippet

የሶፍትዌሮችን ወቅታዊነት መጠበቅ

ብዙውን ጊዜ የኮምፒውተር ፕሮግራሞች ትልቅና ውስብስብ ናቸው። አዘውትረን የምንጠቀምባቸውነ አንዳንድ ሶፍትዌሮች ያልተደረሰባቸው ጉድለቶች አሉባቸው፤ ከእነዚህ ጉድለቶች የተወሰኑት ደግሞ ኮምፒውተሮቻችንን ለአደጋ ሊያጋልጡ የሚችሉ ናቸው። ሶፍትዌር ፈጣሪዎች እነዚህን ጉድለቶችና ክፍተቶች በማግኘት ላይ ናቸው፤ ክፍተቶቹን የሚሞሉ ማሻሻያዎችንም በየጊዜው በመሥራት ለተጠቃሚዎች ያቀርባሉ። ሆኖም በኮምፒውተራችን ላሉ ሶፍትዌሮች በየጊዜው የሚዘጋጁ ማሻሻያዎችን (update) መጫን እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። የተሻሻሉ የኮምፒውተር ኦፐሬቲንግ ሲስተም (operating system) አይነቶችንም መጫን ያስፈልጋል። ዊንዶውስ በቀጥታ ማሻሻያዎችን የማይጭን ከሆነ ይህን ማስተካከል እንችላለን። ይህን ለመቀየር ወደ ስታርት (Start) ሜኑ በመግባት፣ ኦል ፕሮግራምስን (All Programs) መምረጥ፣ ከዚያም ዊንዶውስ አፕዴትን (Windows Update) መጫን። ይህ በቀጥታ ኢንተርኔት ኤክስፕሎረርን ይከፍታል፤ ከዚያም ኮምፒውተራችን በቀጥታ የተሻሻሉ ሶፍትዌሮችን እንዲቀበል (Automatic Updates) የሚያስችለውን ማስተካከያ ወደምናደርግበት የማይክሮሶፍት አፕዴት ገጽ (Microsoft Update page) ያመራናል። የበለጠ ለመረዳት ተጨማሪ ንባብ ክፍሉን ይመልከቱ።

የተሻሻሉ ነጻ ሶፍትዌሮችን እና ኤፍኦኤስኤስ መሣሪያዎችን በወቅቱ ማግኘት

ፈቃድ የሚፈልጉ ሶፍትዌሮች (Proprietary software) ወቅታዊ ማሻሻያዎችን (updates) በኮምፒውተራችን ላይ ከመጫናችን በፊት በሕጋዊ መንገድ የተገዙ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ይጠይቃሉ። ለምሳሌ በሕገወጥ መንገድ የተባዛ የማይክሮሶፍት ዊንዶውስ ቅጂ ብንጠቀም ወቅታዊ ማሻሻያዎችን በየጊዜው ለመቀበል ስለማንችል መረጃችን ለአደጋ የተጋለጠ ይሆናል። ሕጋዊ የመገልገል መብት/ፈቃድ ከሌለን ራሳችንን እና ሌሎችንም ለጉዳት እናጋልጣለን። ሕጋዊ ባልሆኑ ሶፍትዌሮች ላይ መተማመን ቴክኒካል ያልሆኑ አደጋዎችን ሊያስከትልብንም ይችላል። ድርጅቶች የሚጠቀሙባቸው እያንዳንዳቸው ሶፍትዌሮች ሕጋዊ መሆናቸውን መፈተሽ የጀመሩ አገሮች አሉ። ቁጥራቸው እየጨመረ በመጣው በእነዚህ አገሮች ፖሊስ “በሶፍትዌር መብቶች ስርቆት” ('software piracy') ኮምፒውተሮችን ይወርሳል፣ ድርጅቶችን ይከሳል። ይህ አሠራር በድርጅቶች ውስጣዊ ሥራ ጣልቃ ለመግባት የሚፈልጉ መንግሥታት ባሉባቸው አገሮች በቀላሉ የፖለቲካ መጠቀሚያ ሊሆን ይችላል። ደግነቱ ከዚህ መሰሉ ነገር ለማምለጥ በውድ ዋጋ የሚሸጡ ሶፍትዌሮችን መግዛት አያስፈልገንም።

ፈቃድ የሚፈልጉ ሶፍትዌሮች (Proprietary software) ወይም የተሰረቁ ፕሮግራሞችን ከመጠቀም ይልቅ ነጻ ሶፍትዌሮችን (freeware) ወይም ነጻና ክፍት ሶፍትዌሮችን (ኤፍኦኤስኤስ/FOSS) እንድንጠቀም ባለሞያዎች ይመክራሉ። ነጻ ሶፍትዌሮች (freeware) ወይም ኤፍኦኤስኤስ (FOSS) መሣሪያዎች አብዛኛውን ጊዜ በበጎ ፈቃደኛ ባለሞያዎች እና ለትርፍ በማይሠሩ ድርጅቶች የሚፈጠሩና ለተገልጋዮች በነጻ የሚቀርቡ ናቸው። ማሻሻያቸውም እንዲሁ በነጻ የሚቀርቡ ናቸው። ኤፍኦኤስኤስ (FOSS) ፕሮግራሞች የገንዘብ ክፍያም ሆነ ለመጠቀም ቴክኒካዊ ቅድመ ሁኔታ የማያስቀምጡ ናቸው፤ ቀመራቸውም ለሕዝብ የተገለጠ ነው። ነጻ ሶፍትዌሮችን (freeware) የምንላቸው ለመጠቀም ክፍያ ባይጠይቁም ቀመራቸውን ለመደበቅ ቴክኒካዊና ሕጋዊ ቅድመ ሁኔታዎችን ያስቀምጣሉ። ኤፍኦኤስኤስ (FOSS) መሣሪያዎች በአብዛኛው ፈቃድ ከሚፈልጉ ሶፍትዌሮች (Proprietary software) በተሻለ አስተማማኝ ናቸው። የዚህ ዋና ምክንያትም ኤፍኦኤስኤስ (FOSS) መሣሪያዎች የተሠሩበት መሠረታዊ የኮምፒውተር ቀመር/ኮድ (source code) ለማንም ምርመራ ክፍት በመሆናቸው በብዙ ባለሞያዎች ፍተሻ ስለሚደረግባችው ነው፤ በብዙ ባለሞያዎች ለብዙ ጊዜ በተፈተሹ መጠንም ድክመታቸው ስለሚገኝ የማያቋርጥ ማሻሻያ ይደረግባቸዋል።

በግዢ የሚገኙትን ሶፍትዌሮች ለመተካት የሚዘጋጁት ብዙዎቹ ኤፍኦኤስኤስ (FOSS) መሣሪያዎች ተመሳሳይ ሥራ፣ በተመሳሳይ መንገድ ይሠራሉ። እነዚህን ፕሮግራሞች ዊንዶውስን ጨምሮ በግዢ ከሚገኙት ሌሎች ሶፍትዌሮች ጋራ በጥምረት መጠቀም ይቻላል። የሥራ ባለደረቦቻችን በግዢ የሚገኙ ሶፍትዌሮችን መጠቀማቸውን ቢቀጥሉ እንኳን ፋይሎችን መለዋወጥና ያለችግር በጋራ መጠቀም እንችላለን። ስለዚህ እንደቅደም ተከተላቸው ኢንተርኔት ኤክስፕሎረር (Internet Explorer)፣ አውትሉክ ወይም አውትሉክ ኤክስፕረስ (Outlook or Outlook Express) እና ማይክሮሶፍት ኦፊስን (Microsoft Office) በፋየርፎክስ (Firefox)፣ በተንደርበርድ (Thunderbird) እና በኦፕንኦፊስ (OpenOffice) መተካትን ልናስብበት ይገባል።

በዚህም ሳናበቃ ከማይክሮሶፍት ዊንዶውስ ሲስተም (Microsoft Windows operating system) በመውጣት የተሻለ ጥበቃ የሚያደርጉትን ኤፍኦኤስኤስ (FOSS) አማራጭ የሆነውን ጂኤንዩ/ሊኑክስ (GNU/Linux) መሞከር እንችላለን። ይህን ለውጥ ለማድረግ ዝግጁ መሆን አለመሆናችንን ለማረጋገጥ ቀላሉ ዘዴ መሞከር ነው። በኡቡንቱ ሊኑክስ (Ubuntu Linux) ከኢንተርኔት ወደሲዲ ወይም ዲቪዲ መቅዳት እንችላለን፤ ከዚያ በኮምፒውተራችን አድርገን እንደገና ማስጀመር (ሪስታርት) ነው። ኮምፒውተሩ ጭኖ ሲጨርስ ጂኤንዩ/ሊኑክስ (GNU/Linux) ለአገልግሎት ዝግጁ ይሆናል፤ ከዚያ ምርጫው የግላችን ነው። ብዙ የሚያስጨንቅ ነገር የለውም። ስንጨርስ ላይቭ ሲዲውን አውጥተን ኮምፒውተራችንን ማጥፋት ነው። በሚቀጥለው ኮምፒውተራችንን ስንከፍት ወደዊንዶውስ እንመለሳለን፤ ሁሉንም ነገር እንደነበረ እናገኘዋለን። ነጻ ሶፍትዌሮች በአጠቃላይ ከሚሰጡት የተሻለ የደኅንነት ጥበቃ በተጨማሪ የኡቡንቱ (Ubuntu) መሻሻያ የተደረገባቸውን ነገሮች በቀጥታ በመጫን ብዙዎቹ ሶፍትዌሮቻችን ቀን እንዳያልፍባቸውና አስተማማኝ ሆነው እንዲቆዩ ያደርግልናል። ይህም በነጻ የሚገኝ አገልግሎት መሆኑ የበለጠ ተመራጭ ያደርገዋል።

ተጨማሪ ንባብ