10. ደኅንነቱ የተጠበቀ የተንቀሳቃሽ (ሞባይል) ስልኮች አጠቃቀም

Updated2013

መመሪያው በወቅቱ አልተሻሻለም፤ በቅርቡ ይሰረዛል

ተንቀሳቃሽ ስልኮች በእለታዊ ግንኙነታችን ውስጥ ወሳኝ ሚና ያላቸው ቁሶች። ሁሉም ሞባይሎች ድምጽን እና አጭር የጽሑፍ መልእክቶችን (ቴክስት) የማስተላለፍ አቅም አላቸው። በመጠናቸው አነስተኝነት፣ በዋጋቸው አንጻራዊ ርካሽነት፣ እንዲሁም በርካታ አገልግሎቶችን የሚሰጡ በመሆናቸው የመብት ተሟጋቾች በብዛት እየተጠቀሙባቸው ይገኛል፤ ለግንኙነት እና ለማደራጀት ሥራዎችም ይጠቀሙባቸዋል።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ ተጨማሪ አገልግሎቶችን የሚሰጡ የተንቀሳቃሽ ስልክ አይነቶች እየቀረቡ ነው። ጂፒኤስ (GPS)፣ መልቲ ሚዲያ (ፎቶ፣ ቪዲዮ እና ድምጽ መቅዳትና ማስተላለፍ)፣ ዳታ ማቀናበር እና የኢንተርኔት ግንኙነትን ሁሉ ከእነዚህ ስልኮች ማግኘት ይቻላል። ይሁንና የእነዚህ ስልኮች መረብ የሚሠራበት (operate) መንገድ እና መሠረታዊ መዋቅሩ (infrastructure) ኢንተርኔት ከሚንቀሳቀስበት ሁኔታ ጋራ በመሠረቱ የተለየ ነው። ይህም ተጨማሪ የደኅንነት ተግዳሮቶችን ያስከትላል፤ የተጠቃሚዎች ምሥጢራዊነት፣ የመረጃዎቻቸው እና የግንኙነታቸው ጥበቃ አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል።

አስረጅ አጋጣሚ

:Snippet

የምእራፉ ዋና ዋና ጭብጦች

 • በሞባይል ስልክ የሚደረጉ ግንኙነቶች እና በስልኩ ላይ የሚጠራቀሙ መረጃዎች ደኅንነታቸው የተጠበቀ የማይሆነው ለምንድን ነው?
 • የሞባይል ስልኮች አጠቃቀማችንን ደኅንነት ለማሻሻል ምን እርምጃዎች መውሰድ እንችላለን?
 • በሞባይል ስልኮቻችንን ልንሰለል ወይም ያለንበት ቦታና እንቅስቃሴያችን በክትትል ስር ሊወድቅ ይችላል፤ የዚህን እድል መቀነስ የምንችለው እንደምን ነው?
 • ስልኮቻችንን ስንጠቀም ማንነታችንን ለመሰወር ያለንን እድል ለማስፋት ምን ማድረግ እንችላለን?

ተንቀሳቃሽ ስልኮች እና ደኅንነት

ተንቀሳቃሽ ስልኮቻችንን ስንጠቀም ራሳችንን፣ የምንገናኛቸውን ሰዎች እና በስልኩ ውስጥ የያዝነውን መረጃ ለመጠበቅ የሚያስችል በእውቀት ላይ የተመሠረተ ውሳኔ መስጠት አለብን። የተንቀሳቃሽ ስልኮች ኔትወርክ እና መሠረታዊ መዋቅር በተጠቃሚዎች የመረጃ ደኅንነት እና ምሥጢራዊነት ላይ ጉልህ አሉታዊ ተጽእኖ ያስከትላል።

 • የሞባይል ኔትወርኮች ለትርፍ በሚሠሩ ድርጅቶች የሚዘረጉ ናቸው፤ በአንዳንድ አገሮች እነዚህ ድርጅቶች በመንግሥት ሞኖፖሊ የተያዙ ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህ ድርጅቶች ወይም መንግሥት የተጠቃሚዎችን መረጃና ግንኙነት ለማወቅ፣ ጥሪዎቻቸውንና የጽሑፍ መልክእቶቻቸውን ለመጥለፍ፣ እንዲሁም የሞባይል ስልኮቹ ያሉበትን ቦታ ለመከታተል የሚችሉበት ያልተገደበ አቅም አላቸው።

 • የሞባይል ስልኮች የሚሠሩበት “ኦፕሬቲንግ ሲስተም” ከተለያዩ ኔትወርኮች ጋራ ተግባብቶ እንዲሠራ በራሳቸው በስልክ አምራቾቹ የተነደፈ (ዲዛይን የተደረገ) ነው። በውጤቱም የስልኮቹ ኦፕሬቲንግ ሲስተም አገልግሎት ሰጪዎቹ ማንኛውንም ስልክ ወይም መሰል መሣሪያ (device) በቀላሉ እንዲቆጣጠሩት (monitoring) የሚያስችላቸው የተደበቁ አሠራሮች/አገልግሎቶች ሊኖረው ይችላል።

 • ባለፉት ጥቂት ዓመታት ተንቀሳቃሽ ስልኮች የሚሰጡት አገልግሎት ብዛት እየጨመረ ነው። ዘመናዊ ሞባይል ስልኮች ከኢንተርኔት ጋራ መገናኘት የሚችሉ፣ የስልክ አገልግሎቶችን የሚሰጡ አነስተኛ ተንቀሳቃሽ ኮምፒውተሮች ሆነዋል።

የትኛው የግንኙነታችን አይነት የበለጠ ጥበቃና ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገው ለመወሰን እንዲረዳን ጥቂት ጥያቄዎችን መመለስ ይኖርብናል። የስልክ ጥሪዎቻችን እና የጽሑፍ መልእክቶቻችን ይዘት ምንድን ነው? መቼ እና ከእነማን ጋራ ነው የምንገናኝባቸው? ጥሪዎቻችንን የምናደርገው የት ሆነን ነው? መረጃዎች በብዙ መንገድ ለአደጋ የተጋለጡ ናቸው፤

 • መረጃ ከሞባይ ስልክ ሲላክ ለአደጋ ተጋልጧል
  ምሳሌ፦ እያንዳንዱ የሞባይል ስልክ አገልግሎት ሰጪ በእርሱ ኔትወርክ የሚያልፉ ማናቸውንም የድምፅና የጽሑፍ መልእክቶች ሙሉ በሙሉ ያውቃቸዋል፣ ያገኛቸዋል። በብዙ አገሮች የሞባይል ስልክ አገልግሎት ሰጪዎች ሁሉንም ግንኙነቶች መዝግበው እንዲያስቀምጡ በሕግ ይገደዳሉ። በአንዳንድ አገሮች ደግሞ ጭራሹንም የስልክ አገልግሎት በመንግሥት ሙሉ ቁጥጥር (ሞኖፖሊ) ስር ነው። የድምጽ እና የጽሑፍ ልውውጦች በሌላ ሦስተኛ ወገንም በቀላሉ ሊጠለፉ ይችላሉ፤ ይህን ለማድረግ የሚያስችለው መሣሪያም ብዙ ዋጋ የሚያስወጣ አይደለም።

 • መረጃዎች በላኪው እና በተቀባዩ ስልኮች ውስጥ እያሉም ለአደጋ የተጋለጡ ናቸው
  ምሳሌ፦ ተንቀሳቃሽ ስልኮች ብዙ አይነት መረጃዎችን ያጠራቅማሉ፤ የጥሪ ዝርዝር/ታሪክ (call history)፣ የተላኩ እና የመጡ የጽሑፍ መልእክቶች፣ የአድራሻ መዝገብ (address book)፣ ፎቶዎች፣ ቪዲዮዎች እና ፋይሎች ያጠራቅማሉ። እነዚህ መረጃዎች በራሳቸው የምናገኛቸውን ሰዎች ማለትም የግል የግንኙነት መረባችንን፣ ስለራሳችንና ሰለባልደረቦቻችን/ጓደኞቻችን የያዝናቸውን ግላዊ መረጃዎች ሁሉ ሊያጋልጡ የሚችሉ ናቸው። እነዚህን መረጃዎች መጠበቅ በጣም አስቸጋሪ ነው፤ በአንዳንድ ስልኮች ላይ ደግሞ ፈጽሞ የማይቻልም ነው። ዘመናዊዎቹ ስልኮች በኪስ ልክ የተሰሩ ኮምፒውተሮች ናቸው። ስልኮቹ የሚሰጡት አገልግሎት አይነት በጨመረ መጠን አደጋውም እያደገ ይሔዳል። ከኢንተርኔት ጋራ የሚገናኙት ስልኮች ደግሞ ከኮምፒውተር እና ከኢንተርኔት ጋራ የሚመጣው የደኅንነት አደጋ ተጋላጮች መሆናቸው የማይቀር ነው።

 • ስልኮች ስለሚገኙበት ቦታ/አካባቢ መረጃ ያስተላልፋሉ
  ምሳሌ፦ ሁሉም ተንቀሳቃሽ ስልኮች ያሉበትን ቦታ በቋሚነትና በየጊዜው ለአገልግሎት ሰጪው ያስታውቃሉ፤ ይህም የማይቋረጥ መደበኛ የሥራው ሒደት ነው። ይብሱንም ደግሞ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሚመረቱት ስልኮች የጂፒኤስ (GPS) አገልግሎት ይሰጣሉ። ይህም ስልኩ በማንኛውም ቅጽበት የነበረበትን ትክክለኛ ቦታ በፎቶዎች፣ በአጭር መልእክቶች ወይም ከስልኩ በተላከ የኢንተርኔት ግንኙነት ጥያቄ ውስጥ በድብቅ እንዲጻፍ (embedded) ሊያደርግ የሚችል ነው።

የቴክኖሎጂ አዝጋሚ ለውጥ ብዙ ተጨማሪ አገልግሎቶችን አስገኝቷል፤ ነገር ግን አደጋውም ጨምሯል

:Snippet

ሞባይል ስልኮችን ከመጠቀም ጋራ ተያይዘው ሊመጡ የሚችሉ የደኅንነት አደጋዎችን ለመቀነስ የሚያስችሉንን ቀላል የጥንቃቄ እርምጃዎች በሚቀጥሉት ክፍሎች እናገኛለን።

ተንቀሳቃሽነት እና የመረጃዎች ተጋላጭነት

ሰዎች ስሱ መረጃዎችን የያዙ ሞባይል ስልኮችን ይዘው ከቦታ ቦታ ይዘዋወራሉ። በስልኮቹ ውስጥ የግንኙነት ታሪካችን፣ የጽሑፍ እና የድምጽ መልእክቶች፣ አድራሻዎች፣ የቀን ማውጫና እቅድ፣ ፎቶዎች እና ሌሎችም ጠቃሚ መረጃዎች ያሉበት ስልክ ቢጠፋ ወይም ቢሰረቅ ጉዳቱ ከፍተኛ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ከሞባይል ስልካችን ላይ የተጠራቀመውን መረጃ ምንነት ለይቶ ማወቅ በጣም አስፈላጊ ነው። ምናልባትም በሞባይል ስልክ ውስጥ የተጠራቀመ መረጃ የስልኩን ባለቤት እና በስልኩ ውስጥ አድራሻቸው፣ መልእክታቸው፣ ፎቷቸው ወዘተ የተገኘ ሰዎችን ጭምር ለአደጋ ሊዳርግ የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል።

ቀደም ሲል እንደጠቀስነው ከኢንተርኔት ጋራ የሚገናኙ ስልኮች ሁሉ ከኢንትርኔት እና ከኮምፒውተር ጋራ ተያየዘው ለሚመጡ አደጋዎች ይጋለጣሉ። ቀደም ባሉት ምእራፎች የተነሡት የመረጃ ደኅንነት፣ ማንነትን መሰወር፣ የጠፉ መረጃዎችን መልሶ ማግኘት፣ ጠለፋና ስለላ በእነዚህ ስልኮች ላይ ሊተገበሩ ይችላሉ።

እነዚህን አደጋዎች ለመቀነስ የምንገለገልባቸውን ስልኮች ደካማ ጎን እና የሚያቀርቡትን የደኅንነት ጥበቃ አማራጮች (set-up options) ማወቅ ይጠበቅብናል። ሊፈጠሩ የሚችሉትን የደኅንነት ችግሮች አስቀድመን ካወቅን የሚቻለውን የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃ ሁሉ በወቅቱ ለመውሰድ እንችላለን።

:Snippet

የስልክ ደኅንነት ጥበቃ ማሳያዎች

እንደማንኛውም መሰል መሣሪያ፣ የሞባይል ስልክ ደኅንነት ጥበቃ የመጀመሪያ እርምጃ የስልኩን እና የሲም ካርዱን (SIM card) አካላዊ ደኅንነት ማለትም እንዳይሰረቅ ወይም እንዳይጎዳ መጠበቅ ነው።

 • ስልኮቻችንን ምንግዜም ከእኛ አንለያቸው፤ የትም ቦታ ቢሆን ትተናቸው አንሒድ። ስልክን በየአደባባዩ “እዩልኝ” ማለትም የሚመከር አይደለም።

 • የስልካችንን የምሥጢር መቆለፊያ ወይም ፒን ቁጥር (Personal Identification Numbers-PINs) ሁልጊዜም መጠቀም፤ የይለፍ ቃሉንም ለማንም አለማሳወቅ የጠንቃቃነት ምልክት ነው። ፋብሪካው የሚያስቀምጠውን “የተለመደ” ምርጫ (default factory settings) መቀየር ያስፈልጋል።

 • በሲም እና በሜሞሪ ካርዶች፣ በባትሪ እና በስልኩ በራሱ ላይ ሌሎች ብዙም የማያስተውሉት እኛ ግን በደንብ የምንለየው አካላዊ ምልክት ማድረግም የሚመከር ነው። ይህም ላያቸው ላይ መጻፍ፣ የሚለጠፍ ነገር ማድረግ፣ በቀጥታ የማይታዩ መጻፊያዎችን መጠቀም ወዘተ ሊሆን ይችላል። በስልኩ ማእዘን/ማእዘኖች ላይ ፕላስተር ወይም መሰል ነገር መለጠፍ/ማጣበቅም ይቻላል፤ የስልኩን ውስጥ ለመክፈት ወይም ለመቀየር ሙከራ ቢደረግ እነዚህ የተለጠፉ ነገሮች ተዛብተው ስለምናገኛቸው ፍንጭ ሊሰጡን ይችላሉ።

 • በስልኩ በራሱ ላይ፣ በሲም ካርዱ እና በሜሞሪ ካርዱ ላይ ያጠራቀምናቸውን መረጃዎች ምንነት ለይቶ ማወቅም አስፈላጊ ነው። ስሱ መረጃዎችን ስልኩ ላይ ማስቀመጥ የለብንም። ስሱ መረጃዎቸን በቋሚነት ማስቀመጥ ከፈለግን በሚነቀሉ ሜሞሪ ካርዶች ላይ ማድረግ ይመረጣል፤ አስፈላጊ ሲሆን እነዚህን ካርዶች ማጥፋት ቀላል ነው። በስልኩ ውስጣዊ ሜሞሪ ላይ እነዚህን መረጃዎች ማስቀመጥ አይመከርም።

 • ሲም ካርዶችን እና በተጨማሪ የምንጠቀምባቸውን ሜሞሪ ካርዶች በጥንቃቄ መጠበቅ አለብን፤ ካርዶቹ የአጭር መልእክት ልውውጦችን ጨምሮ ስሱ መረጃዎችን ሊይዙ ይችላሉ። ለምሳሌ ስልኩን ለማሳደስ ስንሰጥ እነዚህን ካርዶች አውጥትን መያዝ አለብን።

 • ስልክ ስንቀይር በስልኩ፣ በሲሙ እና በሜሞሪ ካርዶቹ ውስጥ መረጃ አለመተዋችንን ማረጋገጥ በጣም አስፈላጊ ነው። ስልኩ ወይም ካርዶቹ ተሰብረው ቢሆን እንኳን የያዙት መረጃ መልሶ ሊገኝ ስለሚችል መጠንቀቅ አለብን። ሲም ካርዶችን አደቃቆ መሰባበር አንድ መፍትሔ ነው። ስልኩን በስጦታም ይሁን በሽያጭ ለሌላ ሰው አሳልፈን የምንሰጠው ከሆነም መረጃዎቹን በሙሉ መደምሰሳችንን (delete) ማረጋገጥ ይኖርብናል።

 • ለግዢም ሆነ ለእድሳት የምንመርጣቸው ሱቆች የሚታመኑ መሆናቸውን ማረጋገጥ ጠቃሚ ነው። ስልካችንን ከማንኛውም ሱቅ የምንገዛ ከሆነ ስልኩ አስቀድሞ የስለላ ሶፍትዌር ተገጥሞለት ሊሸጥልን ይችላል።

 • በስልካችን ላይ ያለንን መረጃ መጠባበቂያ ቅጂ ወደ ኮምፒውተር መገልበጥ፤ ይህን መጠባበቂያ ክምችት አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ መጠበቅ ተገቢ ነው። ስለዚህ በምእራፍ 4. በኮምፒውተራችን ውስጥ ያሉ ስሱ መረጃዎችን እንዴት መጠበቅ ይቻላል? የተዘረዘረውን መመልከት ይቻላል። ይህ ክምችት ስልካችን ቢጠፋብን መረጃውንም አብረን እንዳናጣ ይረዳናል። በተጨማሪም መጠባበቂያ ክምችቱ ስልካችን ቢጠፋ ወይም ቢሰረቅ፣ ይዞብን የሄደውን መረጃ ምንነት ለማረጋገጥ ይረዳናል፤ ከዚህ በመነሣት አስፈላጊነው እርምጃ ለመውሰድ እንችላለን።

 • ባለ 15 አሐዙ ዓለም አቀፍ የሞባይል መሣሪያ መለያ (International Mobile Equipment Identity-IMEI) ቁጥር ስልካችንን ለመለየት ሊረዳን ይችላል። በብዙ ስልኮች *#06# በማስገባት የስልኩን የመለያ ቁጥር ማግኘት ይቻላል። የባትሪያችንን ጀርባ በመመልከት፣ እንዲሁም የስልኩን ሴቲንግ (settings) በማየትም ስልካችንን ለመለየት እንችላለን። ይህን ቁጥር በሌላ ቦታ መዝግቦ መያዝ፣ ባስፈለገ ጊዜ ስልኩ የእኛ መሆኑን ለማረጋገጥ ሊጠቅመን ይችላል።

 • የስልክ ካምፓኒው/ቴሌ ስልኩን በስማችን እንዲመዘግበው ማድረግ ያለውን ጥቅምና ጉዳት አስቀድሞ ማሰብ ይመከራል። ስልኩ በስማችን ከተመዘገበ፣ ስልኩ ቢጠፋብን ሌሎች እንዳይጠቀሙበት ለማስጠፋት እንችላለን። ሆኖም ስልኩ በስማችን ተመዘገበ ማለት በስልኩ የምናደርገው ግንኙነት ሁሉ የእኛ መሆኑ በቀላሉ ይታወቃል ማለት ነው።

መሠረታዊ አገልግሎቶች፣ ክትትል እና ማንነትን መደበቅ

በስልካችን ጥሪ ለማድረግ ወይም ለመቀበል፣ ወይም ስልካችን አንዳች አይነት ግንኙነት ለማድረግ ሲፈልግ በአቅራቢያችን የሚገኙት የሲግናል ማማዎች (signal towers) ለስልካችን ምልክት ይሰጡታል። በእነዚህ ማንቂያዎች እና ግንኙነቶች አማካይነት የኔትወርኩ አገልግሎት ሰጪ ሞባይል ስልካችን በየትኛው ጊዜ የት ቦታ እንዳለ በትክክል ለማወቅ ይችላል።

:Snippet

ማንነትን መደበቅ

ስሱ የስልክ ንግግሮችን የሚያደርጉ ወይም ስሱ አጭር መልእክቶችን የሚለዋወጡ ሰዎች ቀደም ሲል የተብራራውን የሞባይል ስልኮች ለክትትል የመጋለጥ ጉዳይ ሊያስታውሱ ይገባል። የሚከተሉትን የጥንቃቄ እርምጃዎች መከተሉ አይከፋም፤

 • ጥሪዎችህን በተቻለ መጠን ከተለያየ ቦታ አድርግ፤ አንተ ትገኝበታለህ ተብለው የማይታሰቡ ቦታዎችን ምረጥ፤
 • ወደ መረጥከው ቦታ ከመንቀሳቀስህ በፊት ስልክህን አጥፋ፣ ባትሪውን አውጣ። በቦታው ደርሰህ ጥሪውን ካደረክ በኋላ በተመሳሳይ መንገድ ስልክህን አጥፍተህ ባትሪውን አውጣው። ይህን በመደበኛነት መተግበር ቻልክ ማለት ኔትወርኩ እንቅስቃሴህን እንዳይከታተል አደረከው ማለት ነው፤
 • በተቻለ መጠን ስልክህንና ሲም ካርዱን (SIM card) ቶሎ ቶሎ ቀይር። ከሌሎች ሰዎች ጋራ ተለዋወጠው ወይም ባገለገሉ እቃዎች ገበያ ሽጠህ ሌላ ግዛ፤
 • በስምህ ያልተመዘገበ፣ የቅድመ ክፍያ ሲም ካርድ ተጠቀም፤
 • የክሬዲት ካርድ ተጠቃሚ ከሆንክ፣ ለስልክም ይሁን ለሲም ካርድ በክሬዲት ካርድህ አትክፈል። ይህ ክፍያ በአንተ እና በገዛኸው ነገር መካከል ግንኙነት መኖሩን ይመዘግባልና።

:Snippet

የስልክ ንግግሮችን ጣልቃ ገብቶ ማዳመጥ (ጆሮ መጥባት)

ሞባይል ስልኮች እኛ ሳናውቀው በአካባቢያቸው ያለውን ድምጽ ሊቀዱና ሊያስተላልፉ የሚችሉበት እድል አለ። አንዳንድ ስልኮች እንዲያውም እኛ ያጠፋናቸው መስሎን ከርቀት ሊበሩ/ሊከፈቱ እና ይህንን ድምፅ የማስተላለፍ ሥራቸውን ሊቀጥሉ ይችላሉ።

 • በሚገባ የማናምናቸው ሰዎች ስልካችንን ለተወሰነ ደቂቃም ቢሆን እንዲይዙ መፍቀድ የለብንም። የስለላ ሶፍትዌሮችን ወደ ስልኮች ለመጫን በጣም የተለመደው መንገድ ይህ የጥቂት ደቂቃዎች እድል ማግኘት ነው።
 • እጅግ አስፈላጊ እና ግላዊ ስብሰባዎችን በምናደርግ ጊዜ ስልኮቻችንን ማጥፋት እና ባትሪ መንቀል አስፈላጊ ነው። ስልኩን ሌላ ቦታ ትቶ መሔድ አስተማማኝ ከሆነ ከነጭራሹ አለማምጣት ይመረጣል።
 • አብረናቸው የምንሠራ እንዲሁም የምንገናኛቸውን ሰዎች ተመሳሳይ የጥንቃቄ እርምጃ እንዲወስዱ ማድረግ የግድ ነው።
 • ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች በስልክ ስሱ ጉዳዮችን መነጋገር ለተለመደው የስለላ (የጆሮ መጥባት) ስልት ሊያጋልጠን እንደሚችል አለመዘንጋት ነው፤ አልፎም ስልካችንን መስረቅ ለሚፈልጉ እድል ሊሰጥ ይችላል።

የስልክ ጥሪዎችን መጥለፍ

በሞባይል ስልክ ኔትወርክ የሚያልፉ የድምጽ እና የጽሑፍ መልእክቶችን ኢንክሪፕት/ስውር ማድረግ በአንጻራዊነት ደካማ ነው። በስልኩ አቅራቢያ ከሆኑ የድምጽና የጽሑፍ መልእክቶችን ለመጥለፍ የሚያስችሉ፣ ሦስተኛ ወገኖች በርካሽ ዋጋ ሊያገኙዋቸው የሚችሉ ዘዴዎች/መሣሪያዎች አሉ። የሞባይል አገልግሎት ሰጪዎች የምናደርጋቸውን ግንኙነቶች በሙሉ ማግኘት እንደሚችሉ በተደጋጋሚ ጠቅሰናል። አሁን ያለው የስልክ ጥሪዎችን ኢንክሪፕት ለማድረግና አገልግሎት ሲጪዎቹ ንግግሮቻችንን እንዳያዳምጡ የሚያደርገው ቴክኖሎጂ ውስብስብና ብዙ ወጪ የሚጠይቅ ነው፤ ነገር ግን በቅርቡ ቴክኖሎጂው ተሻሽሎ በርካሽ እንደሚቀርቡ ይጠበቃል። አሁን ኢንክሪፕሽን መጠቀም ከፈለግን መጀመሪያ አፕሊኬሽኑን በስልካችን ላይ መጫን አለብን፤ በተመሳሳይም በስልክ ልናነጋግረው የፈለግነው ሰውም በተመሳሳይ የኢንክሪፕሽን አፕሊኬሽኑን መጫን ይኖርበታል። ከዚያ ኢንክሪፕት የተደረጉ ጥሪዎችን እና/ወይም የጽሑፍ መልእክቶችን ለመለዋወጥ ልንጠቀምበት እንችላለን። ይህ የኢንክሪፕሽን ሶፍትዌር የሚሠራው “ስማርት ፎን” በሚባሉት የቅርብ ጊዜ ሞዴል ስልኮች ላይ ብቻ ነው።

በስካይፕ እና በስልክ መካከል የሚደረጉ ንግግሮች ኢንክሪፕት የሆኑ አይደሉም፤ ምክንያቱም ኢንክሪፕት የተደረገው መልእክት ወደ ሞባይል ኔትወርክ ሲገባ ስለሚለወጥ ነው፣ ኔትወርኩ ኢንክሪፕት የተደረገ ንግግርን አይቀበልም።

የጽሑፍ መልእክት ልውውጦች - ቴክስት

አጭር የጽሑፍ መልእክቶች ስሱ መረጃዎችን በምሥጢር ለመለዋወጥ የሚያስተማምኑ አይደሉም፤ እኛም ልንተማመንባቸው አይገባም። የመልእክቶቹ ልውውጥ የሚካሔደው እንደ ተራ ጽሑፍ ስለሆነ ምሥጢራዊ መልእክቶችን ለመለዋወጥ የሚሆኑ አይደሉም።

:Snippet

አጭር መልእክቶች በአገልግሎት ሰጪው ወይም ገበያ ላይ በርካሽ የሚገኙ መሣሪያዎችን መጠቀም በሚችል ሦስተኛ ወገን ሊጠለፉ ይችላሉ። መልእክቶቹ የላኪውን እና የተቀባዩን የስልክ ቁጥሮች እና የመልእክቱን ይዘት ያሳያሉ። ከዚህም በላይ ደግሞ አጫጭር የቴክስት መልእክቶች በሦስተኛ ወገኖች በቀላሉ ሊስተካከሉና ሊቀየሩ ይችላሉ።

ስለዚህም ላኪና ተቀባይ የሚግባቡበት ኮድ መፍጠር ጥሩ አማራጭ ነው። ኮዶች የመልእክቱን ምሥጢራዊነት ከፍ ያደርጉታል፤ በተጨማሪም መልእክት ተለዋዋጮቹ ከማን ጋራ እየተገናኙ መሆናቸውን እንዲያረጋግጡ ይረዳቸዋል። የኮድ አሠራር በምሥጢር መያዝ እና በየጊዜው መለዋወጥ እንዳለበት መዘንጋት የለበትም።

የኤስኤምኤስ (SMS) መልእክቶች ከተላለፉ በኋላ ቅጂያቸው ይቀራል

 • በብዙ አገሮች የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት ሰጪዎች ደንበኞቻቸው የተላላኳቸውን የጽሑፍ መልእክቶች ሙሉ ቅጂ ረዘም ላለ ጊዜ እንዲያስቀምጡ በሕግ አውጪው ወይም በሌሎች አካሎች ይገደዳሉ። ብዙውን ጊዜ መልእክቶቹ በአገልግሎት ሰጪው እንዲቀመጡ የሚደረገው ከንግድ፣ ከሒሳብ እና ከሕግ ጋራ ለተያያዙ ጉዳዮች ነው።

 • በስልክ ላይ የተቀመጡ ወይም የተተዉ መልክእቶችን ማንኛውም ስልካችንን በእጁ ማስገባት የቻለ ሰው ሁሉ በቀላሉ ሊመለከታቸው ይችላል። የላክናቸውንም ሆነ የተቀበልናቸውን መልእክቶች ወዲያውኑ ማጥፋት ይመከራል።

 • አንዳንድ ስልኮች የጥሪዎችን እና የጽሑፍ መልእክት ታሪክ/ክምችትን ለመዝጋትና ለመክፈት የሚያስችል አገልግሎት ይሰጣሉ። ጥንቃቄ በሚፈልጉ ሥራዎች የሚሳተፉ ሰዎች ከእነዚህ ስልኮች ብዙ ይጠቀማሉ። ስልኮቻችን ምን አይነት አገልግሎት እንደሚሰጡ በሚገባ ማወቅ በጣም ይጠቅማል። የስልኮቹን የአጠቃቀም መመሪያ (ማኑዋል) ማንበብ ለዚህ ይረዳል።

ከንግግር እና ከጽሑፍ መልእክቶች ውጭ ያሉ አገልግሎቶች

ተንቀሳቃሽ ስልኮች ወደ ተንቀሳቃሽ ኮምፒውተርነት እየተለወጡ ነው። እንዲህ አይነቶቹ ስልኮች የራሳቸው ኦፐሬቲንግ ሲስተም አላቸው፤ የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ እና ዳውንሎድ የሚደረጉ አፕሊኬሽኖችም አሏቸው። በሌላ በኩል፣ ቫይረሶች እና ስፓይዌሮች ወደሞባይል ስልክ ዓለምም መጥተዋል። በስልካችን ውስጥ ቫይረስ ሆን ተብሎ ሊጠመድበት ወይም ከኢንተርኔት ከምንጭናቸው አገልግሎቶች ለምሳሌ የጥሪ ድምፆች፣ መልቲሚዲያ መልእክቶች እና አፕሊኬሽኖች ጋራ ተጣምሮ ሊመጣብን ይችላል።

ቀደም ባሉት ጊዜያት የተመረቱ ሞባይል ስልኮች ከኢንተርኔት ጋራ የተያያዘ አገልግሎት አልነበራቸው፣ ቢኖርም በጣም ውሱን ነበር። ሆኖም ሳናውቀው የስልካችን ደኅንነት አደጋ ውስጥ እንዳይወድቅ ለመከላከል ከዚህ ቀጥሎ የተዘረዘሩትን የጥንቃቄ እርምጃዎች መከተሉ በጥብቅ የሚመከር ነው። አንዳንዶቹ የጥንቃቄ እርምጃዎች “ለስማርት ስልኮች” (Smartphones) ብቻ ሊሠሩ የሚችሉ ቢሆኑም የእያንዳንዳችን ስልክ ምን አገልግሎት እንደሚሰጥና እንደማይሰጥ ማወቅ መውሰድ ያለብንን የመፍትሔ አማራጭ በትክክል እንድንመርጥ ያግዘናል።

 • ምሥጢራዊ ፋይሎችን እና ፎቶዎችን በሞባይል ስልክ ላይ ፈጽሞ አለማስቀመጥ ይመከራል። በተቻለ ፍጥነት ማጥፋት ወይም ወደሌላ አስተማማኝ ቦታ መውሰድ ይገባል፤ በኮምፒውተራችን ውስጥ ያሉ ስሱ መረጃዎችን እንዴት መጠበቅ ይቻላል? የሚለውን ምእራፍ 4 መልሶ መመልከት ይጠቅማል፤

 • የስልክ ጥሪዎን እና የጽሑፍ መልእክቶን ታሪክ/ክምችትን፣ የአድራሻ መዝገቡን፣ ፎቶዎችን ወዘተ ቶሎ ቶሎ ማጥፋት

 • በስልክ ኢንተርኔት የምንጠቀም ከሆነ፣ በኮምፒውተራችን እንደምናደርገው ሁሉ ኢንክሪፕት የተደረገ ግንኙነት ማድረግን አለመርሳት ብልህነት ነው (ለምሳሌ HTTPS መጠቀም)፤

 • ከማልዌር ነጻ መሆኑ ካልተረጋገጠ ኮምፒውተር ጋራ ስልክን አለማገናኘነት። ኮምፒውተርን ከማልዌር እና ከሰርጎ ገቦች ስለመጠበቅ? የሚያወሳውን ምእራፍ 1 ማንበብ፤

 • የማይታወቁ ወይም ትክክለኝነታቸው ያልተረጋገጠ ፕሮግራሞችን ወደ ስልካችን አለመጫን፤ ለምሳሌ የጥሪ ድምፆች (ring tones)፣ የገጽ ምስሎችን (wallpaper)፣ ጃቫ አፕሊኪሽኖችን (java applications)። ከማንፈልጋቸው ወይም ከማይጠበቁ ላኪዎች የሚደርሱ ነገሮችንም እንዲሁ አለመቀበል ነው። እነዚህ ነገሮች ቫይረሶችን፣ የስለላ ፕሮግራሞችን ወዘተ የያዙ ሊሆኑ ይችላሉ፤

 • የስልኮቻችንን የአገልግሎትና የአሠራር ሁኔታ፣ እንዲሁም ለውጦች ማስተዋል። የማናውቃቸው ፕሮግራሞች ሳንከፍታቸው ሲሠሩ ይታያሉ? እንግዳ መልእክቶች ይመጣሉ? ስልኩ ጤና ያጣል? የማንጠቀምባቸውን ወይም የማናውቃቸውን አፕሊኬሽኖችና አገልግሎቶች እንዳይሠሩ ማዘዝ ወይም የተጫነውን ማጥፋት (uninstall)፤

 • የይለፍ ቃል የማይጠይቅ ለሕዝብ ክፍት የሆነ የኢንተርኔት መስመር/ኮኔክሽን ወይም ዋይፋይ (WiFi) መጠቀም ካለብን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። ኮምፒውተር እና ኢንተርኔት የሚገጥማቸው የደኅንነት አደጋ ሁሉ ሞባይል ስልኮችን ሊገጥማቸው እንደሚችል አለመዘንጋት፤

 • በማንጠቀምባቸው ጊዜ ሁሉ የስልኮቻችንን ኢንፍራሬድ (Infrared-IrDA)ብሉቱዝ (Bluetooth) እና ገመድ አልባ/ዋየርለስ (Wireless Internet-WiFi) የኢንተርኔት መስመር አገልግሎቶች ማጥፋት ወይም እንዳይሠራ ማድረግን (switched off and disabled) አለመርሳት። እነዚህን አገልግሎቶች ማብራት ያለብን ልንጠቀምባቸው ስንፈልግ ብቻ መሆን አለበት። በሚታመኑ ሁኔታዎች እና ቦታዎች ብቻ መጠቀምም የሚገባ ነው። ብሉቱዝን ፈጽሞ አለመጠቀም ይመረጣል፤ ለስለላ/ጠለፋ በጣም ቀላል ነውና። መረጃዎችን ከስልክ ወደ ኮምፒውተር ለመውሰድ በብሉቱዝ ከማስተላለፍ ይልቅ ገመዶችን (ኬብሎችን) መጠቀም የተመረጠ ነው።

ተጨማሪ ንባብ