ራይዝአፕ- አስተማማኝ የኢሜይል አገልግሎት

Updated 11 August 2014

መመሪያው በወቅቱ አልተሻሻለም፤ በቅርቡ ይሰረዛል

:Introduction

ዋና ገጽ (Homepage)

https://riseup.net/

ኮምፒውተራችን ምን ያስፈልገዋል?

 • የኢንተርኔት ግንኙነት

 • ራይዝአፕ የበለጠ ውጤታማ ሆኖ የሚሠራው በፋየርፎክስ የመረጃ መረብ ማሰሻ ነው።

በራይዝአፕ ለመጠቀም የሚያስፈልግ ፈቃድ/ላይሰንስ

 • ነጻ ሶፍትዌር (Freeware)

አስፈላጊ ንባብ

 • የኢንተርኔት ደኅንነት መጽሐፍ ምእራፍ [7. የኢንተርኔት ግንኙነታችንን በምሥጢር መያዝ ይቻላል? እንዴት?] (/am/chapter-7)

ይህን መሣሪያ መጠቀም ለመጀመር የሚፈጀው ጊዜ

 • 20 ደቂቃ

ከዚህ መሣሪያ ምን ጥቅም እናገኛለን?

 • የተጠቃሚዎች ማኅበረሰብ ፍላጎት የሚመራው፣ ከማስታወቂያ ነጻ የሆነ የኢሜይል አድራሻ/አካውንት ይኖረናል

 • ኢንክሪፕትድ በሆነ የኢንተርኔት ግንኙነት ምሥጢራዊነቱ አስተማማኝ የሆነ የመረጃ ልውውጥ ለማድረግ እንችላለን፤ የኢሜይል አድራሻችንን በኢንተርኔት ወይም በኢሜይል ፕሮግራም ማግኘት እንችላለን።

 • የኢሜይል አድራሻችንን እንደፈለግን መለወጥ እንችላለን፤ የኤሜይል ሳጥናችንን የመያዝ አቅም መወሰን እንችላለን፤ እንዲሁም ሌሎች ራይዝአፕን እንዲቀላቀሉ መጋበዝ እንችላለን።

አማራጭ የኤሜይል አገልግሎቶች (Alternative Email Services)፦ ምንም እንኳን ራይዝአፕ ለኢንተርኔት ምሥጢራዊነት እና ደኅንነት ቅድሚያ በሚሰጡ አስተማማኝ ብድኖች የሚተዳደር አስተማማኝ የኢሜይል አገልግሎት ቢሆንም በብዙ ተጠቃሚዎች ዘንድ የተለመደ ባለመሆኑ አትኩሮት ሊስብ እንደሚችል መገንዘብ ይገባል። በአንዳንድ ሁኔታዎች ይህን መሰል አዲስ አገልግሎቶችን ከመጠቀም ይልቅ በምንኖርበት አካባበቢ ብዙዎች የሚጠቀሙበትን የኢሜይል አገልግሎት በመጠቀም ራስን መደበቅ የተሻለ ሊሆን ይችላል። ስለዚህም ወደ ራይዝአፕ ተጠቃሚነት ለመምጣት ስንወስን የደኅንነታች ሁኔታ ለአደጋ አለመጋለጡን ማረጋገጥ አለብን። አንድን የኢሜይል አገልግሎት ለመጠቀም ስንወስን የሚከተሉትን ነጥቦች ከግምት እንድናስገባ እንመከራለን፦

 1. አገልግሎቱ ኢንክሪፕት የተደረጉ መንገዶችን በመጠቀም (use of encrypted channels) ማንኛውንም መረጃ ለመለዋወጥ ይፈቅዳልን? ይህ ማለት ለምሳሌ https እና ሌሎችም በኤስኤስኤል (SSL) ኢንክሪፕት የሆኑ እንደ IMAPs ፣ POP3s እና SMTPs የመሳሰሉትን በመጠቀም ኢሜይሎቻችንን ለመክፈት የሚስችሉን መሆናቸው ማረጋገጥ እንደማለት ነው። ከኢንክሪፕሽን ጋራ የተያያዘ ችግር (ለምሳሌ የኢንክሪፕሽን ሰርተፊኬት) እንደሌለበትም ማጣራት ያስፈልጋል።

 2. የኢሜይል አግልግሎቶቹ በአስተማማኝ ሁኔታ የሚተዳደሩና ጥበቃ የሚደረግላቸው ናቸውን? አገልግሎቶቹ የመረጃዎቻችንን ደኅንነት በሚገባ ሊጠብቁ በሚችሉ ባለሞያዎች የሚተዳደሩ ናቸውን? መረጃዎቻችንን በማንኛውም ምክንያት (የንግድ፣ የፖለቲካ፣ የሃይማኖች ወዘተ ጥቅሞች) ለሌላ ሦስተኛ ወገን አሳልፈው እንደማይሰጡ እንተማመንባቸዋል?

 3. አግልግሎት ሰጪው የሚጠቀምባቸው ሰርቨሮች የት እንደሚገኙ፣ በየትኛው አገር ሕግ እንደሚተዳደሩ ወይም ኩባንያው የት እንደተመዘገበ እናውቃለን? ይህ ሁኔታ ከኢሜይሎቻችን እና ከመረጃዎቻችን ምሥጢራዊነትና ጥበቃ ጋራ ያለውን ግንኙነት በሚገባ ተገንዝበናል?

በአንዳንድ አገሮች ጉግል ሜይልን (Google Mail) መጠቀም የመረጃን ጥበቃችንን ደረጃ ብዙ ሳንቀንስ ራይዝአፕን ከመጠቀም በተሻለ ከሌላው ጋራ ተመሳስሎ ከእይታ ለመሰወር የበለጠ የሚመች ነው።

1.1 ይህን መሣሪያ መጠቀም ከመጀመራችን በፊት ልናውቃቸው የሚገቡ ነገሮች

ራይዝአፕ (RiseUp) ለፖለቲካዊና ለማኅበራዊ ፍትሕ ለሚታገሉ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ምሥጢራዊነቱ አስተማማኝ የሆነ የኢሜይል እና የሆስቲንግ አገልግሎት ለመስጠት የቆሙ ድርጅቶች ስብስብ ነው። እነዚህ አገልግሎቶች በነጻ የሚሰጡ በመሆናቸው የኢሜይል አካውንታችን በሚይዘው መረጃ መጠን ከሌሎቹ ጋራ ሲወዳደር አነስተኛ ነው። ይህም የሚሆነው ሌሎቹ በማስታወቂያ ገቢ ጥቅም የሚመሩና ቀዳሚ ግባቸውም የመረጃ ደኅንነት መስጠት ባለመሆኑ ለኢሜይሎች የሚሰጡትን የይዞታ መጠን ከፍ ማድረግ ስለሚችሉ ነው። በራይዝአፕ የኢሜይል አድራሻ/አካውንት ለመክፈት ቀድሞ አባል ከሆነ ወይም ደግሞ በዲጂታል ደኅንነት ፕሮጀክት (Digital Security Project) ተሳታፊ ከሆነ ሰው የግብዣ ኮድ ማግኘት ያስፈልጋል።

ራይዝአፕ ሙሉ በሙሉ የሚሠራው Secure Sockets Layer (SSL) በተባለው ዘዴ ነው። ይህም በራይዝአፕ እና በእኛ ኮምፒውተር መካከል የሚደረገውን ግንኙነት ደኀንነትና ምሥጢራዊነት የሚያረጋግጥ ነው። ጥበቃው ኢሜሎቻችንን ደኅንነታቸው በተጠበቀ የግንኙነት ፕሮቶኮሎች (POP, IMAP and SMTP connections) በኩል የሚደረግ ነው። እነዚህ የኢሜይል ፕሮግራሙ ኢሜይላችንን ከፍተን (download) እንድናነብ የሚያስችሉን ናቸው።

ራይዝአፕ በተለይ ከሞዚላ ታንደርበርድ (Mozilla Thunderbird) ጋራ ይሠራል። በሞዚላ ታንደርበርድ (Mozilla Thunderbird) በኩል የራይዝአፕ የኢሜይል አድራሻችንን እንዴት መክፈት እንደምንችል ለማወቅ ስለ ተንደርበርድ (Thunderbird) የሚያስረዳውን ክፍል ማንበብ ይቻላል።

የራይዝአፕ አድራሻ/አካውንት የሚከፈተው እንዴት ነው?

በዚህ ገጽ የሚዳሰሱ ጉዳዮች፦

2.0 ለራይዝአፕ አድራሻ ለመመዝገብ የሚቻልባቸው መንገዶች

ራይዝአፕ (RiseUp) የኢሜይል አካውንት ለመክፈት ሦስት የተለያዩ አማራጮችን ይሰጠናል። እያንዳንዱ አማራጭ የሚፈልገው ጊዜ እና ጥረት የተለያየ ነው።

 1. ግለሰቦች እና/ወይም ድርጅቶች በሁለት የራይዝአፕ አባላት (account members) ሊጋበዙ ይችላሉ። በዚህ መንገድ አባል ለመሆን ሁለት አባላት የግምዣ ኮድ ሊልኩልን ይገባል። ይህን የግባዣ ኮድ እንዴት ማግኘት/መፍጠር እንደሚቻል ለመረዳት ክፍል 4.3 የመጋበዣ (Invites) ገጽ መመልከት ይጠቅማል።

 2. የራይዝአፕ ቡድን የኢሜይል አድራሻ እንዲሰጠን ወይም በተጠቃሚነት እንዲቀበለን በቀጥታ መጠየቅ። ራይዝአፕ በበጎ ፈቃደኞች እርዳት የሚተደዳደር፣ በበጎ ፈቃደኞች ቴክኒካዊ ድጋፍ የሚሠራ ስለሆነም በዚህ መንገድ የኢሜይል አድራሻ መክፈት የተወሰነ ጊዜ እና ትእግስት ሊጠይቅ ይችላል።

 3. በSecurity in a Box (የዲጂታል ደኅንነት ትጥቅ) ጥቅል ውስጥ በስልጠናው ለሚሳተፉ ተካፋዮች ለእያንዳንዳቸው የግብዣ ኮዱ ይሰጣቸዋል።

የግብዣ ኮድ (invitation code) የደረሰው ሰው የሚከተሉትን ደረጃዎች በመከተል የራይዝአፕ የኢሜይል አድራሻውን በነጻ መክፈትና በአባልነት መመዝገብ ይችላል።

ደረጃ 1፦ ይህንን https://mail.riseup.net አድራሻ በኢንተርኔት ማሰሻችን ላይ በመጻፍ ከታች በስእሉ የሚታየውን የራይዝአፕ ድረ ገጽ መክፈት፤

*ስእል 1፤ የ https://mail.riseup.net/ ገጽ

ማስታወሻhttps:// በሚለው የአድራሻው አካል ውስጥ የምትታየው s ግንኙነታችን Secure Socket Layer (SSL) በሚባለው ዘዴ የተጠበቀ መሆኑን ያሳያል። ከአድራሻ መግቢያችን በላይ ይህን መልእክት ይነበባል። ስለዚህ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የኢንተርኔት ደኅንነት መጽሐፍ ምእራፍ [7. የኢንተርኔት ግንኙነታችንን በምሥጢር መያዝ] (/am/chapter-7) ወይም ደግሞ የራይዝአፕን የኦንላይን መርጃ ክፍል https://help.riseup.net/security መመልከት ነው።

ደረጃ 2Request account ማለትም የአድራሻ/አካውንት መጠየቂያ ገጹን በስእሉ እንደሚታየው ለመክፈት ይህንን ማዘዣ መንካት/ክሊክ

ስእል 2፤ የራይዝአፕ የኢሜይል አካውንት መጠየቂያ ገጽ

ደረጃ 3፦ ወደ ቀጣዩ ደረጃ ለመሔድ ይህንን ማዘዣ መንካት/ክሊክየራይዝአፕ የኢሜይል አገልግሎት እና የአድራሻ መጠየቂያ Request an email account - About our email service ይከፈታል።

ማስታወሻ፦ የኢሜይል አድራሻችንን የመፍጠሩን/የመክፈቱን ሒደት ለመቀጠል የሚከተለው አማራጭ እንዲሠራ መደረግ (enabled) አለበት።

ደረጃ 4ራይዝአፕ የሚጠቀምባቸውን ልዩ ልዩ ፖሊሲዎች ካነበብን በኋላ I accept riseup.net's social contract የሚለውን መምረጥ፤ ከዚያም I accept riseup.net's privacy policy እና I accept riseup.net's terms of service የሚሉትን ምርጫዎች በመንካት/ክሊክ መስማማታችን ማረጋገጥ አለብን።

ደረጃ 5፦ ይህን ማዘዣ መንካት፤ በመቀጠል የራይዝአፕ አድራሻ/አካውንት ለመፍጠር የሚያስፈልጉትን ቅጾች ማለትም Account information* ፣ PasswordMutual aid እና Activation ናቸው።

2.1 የአድራሻ/አካውንት መረጃ ቅጽ (The Account information form)

ደረጃ 6፦ አድራሻውን የሚፈልጉትን የተጠቃሚ ስም መርጦ ማስገባት። ይህ ስም የኢሜይል አድራሻችን መግቢያ (login) ይሆናል። (በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በምንሰጠው ምሳሌ 'ssayyed' በሚለው ስም የሚከፈት የኢሜይል አድራሻን እንጠቀማለን፤ ssayyed@riseup.net )።

ማስታወሻ፦ የተጠቃሚ ስም ስናወጣ በስሙ ውስጥ ኮማ (commas)፣ ነጥብ (full stops) ወይም ባዶ ቦታ (spaces) ማስገባት የለብንም።

ስእል 3፤ የተሟላ የአድራሻ/አካውንት ቅጽ (Account information)

ደረጃ 7፦ የተጠቃሚ ስም ከመረጥን በኋላ የይለፍ ቃል (Password) ቅጽኑ ለማግኘት ይህን ማዘዣ መንካት/ክሊክ

ማስታወሻ፦ እኛ የመረጥነው የተጠቃሚ ስም በሌላ ተጠቃሚ ተይዞ ከሆነ የተለየ ስም እንድንመርጥ የሚያስታውስ መልእክት ይከፈታል።

2.2 የይለፍ ቃል ቅጽ

በይለፍ ቃል ቅጽ ላይ የምሥጢር ጥያቄ እና መልስ መፍጠር አለብን፤ በጣም ጠንካራ የይለፍ ቃልም መፍጠር አለብን። ይህን ካላደረግን ወደቀጣዩ ደረጃ እንድንሸጋገር አይፈቀድልንም። ራይዝአፕ ይህን እንድናደርግ የሚያስበረታታን ምናልባት የይለፍ ቃላችንን ብንረሳው ሊያጋጥመን ከሚችል አደጋ ለመጠበቅ ነው። ሆኖም ይህ ለበጎ ዓላማ ታስቦ የሚደረግ ነገር ያልታሰበ የደኅንነት አደጋ ሊያስከትል መቻሉ ነው።

ለምሳሌ ያህል፣ መረጃችንን ሊሰርቅብን የሚፈልግ ሰው የምሥጢር ጥያቄ መልሳችንን በግምት ሊያገኝብን ወይም ደግሞ አዲስ የተላከልንን አዲስ የይለፍ ቃል በመካከል ሊመነትፍብን ይችላል። ስለዚህም የምስጢር ጥያቄያችን መልስ በተቻለ መጠን የተዘበራረቀ (spoil) ለማድረግ እንድንሞክር እንበረታታለን። ይህን ለማድረግ አንዱ መላ ጥያቄውና መልሱ እንዳይገናኙ ማድረግ ነው። በስእሉ የተሰጠው ምሳሌም ሌላ አማራጭ ነው፤

ስእል 4፤ በይለፍ ቃል ቅጽ የተሞላ የምስጢት ጥያቄ እና የተዘበራረቀ መልስ ምሳሌ

ማስጠንቀቂያ፦ ይህ ማለት የይለፍ ቃላችንን ለመለወጥ የማንችልበት እድል አለ ማለት ነው። የይለፍ ቃላችንን ፈጽሞ መርሳት የለበትም። በጣም አስተማማኙና ቀላሉ አማራጭ ይኸው ነው።

የራይዝአፕ አድራሻችን/አካውንታችን የይለፍ ቃል እጅግ ወሳኙ የደኅንነታችን ማረጋገጫ ነው። አስተማማኝ የይለፍ ቃል ስለመፍጠር የኢንተርኔት ደኅንነት መጽሐፍ ምእራፍ 3. አስተማማኝ የይለፍ (የምሥጢር) ቃል መፍጠር እና መጠቀም እንዲሁም የኪፓስ (KeePass) መመልከት ይቻላል።

ስእል 8፤ የተሟላየይለፍ ቃል ቅጽ

ደረጃ 8፦ ወደ ቀጣዩ የ“mutual aid” ቅጽ ለመሸጋገር ይህን ማዘዣ መንካት/ክሊክ

2.3 የመረዳጃ (Mutual aid) ቅጽ

ራይዝአፕ ሙሉ በሙሉ የተመሰረተው በበጎ አድራጊዎች እና በበጎ ፈቃደኞች ቸርነትና ጽናት ነው። ምንም እንኳን ለዚህ ሥራ የሚቀርብ የገንዘብ እርዳታ ጥያቄ አስፈላጊ እና ሕጋዊ/ሞራላዊ ቢሆንም ራይዝአፕ ተጠቃሚዎቹ ያላቸውን ገንዘብ በአካባቢያቸው ለማኅበራዊ ፍትሕ በሚሰሩ ፕሮጀክቶች ላይ እንዲያውሉም ያበረታታል። እገዛውን ለራይዝአፕ ወይም ለሌላ ድርጅት መስጠት ሙሉ በሙሉ የተጠቃሚዎች ውሳኔ ነው።

ማስታወሻ፦ ይህን እገዛ በተመለከተ የምንሰጠው ውሳኔ ከራይዝአፕ አድራሻችን/አካውንታችን ጋራ ምንም ግንኙነት የለውም። አሁንም በአድራሻው መጠቀማችንን መቀጠል እንችላለን።

ስእል 6፤ የመረዳጃ (mutual aid) ቅጽ

ደረጃ 9፦ የፈጠርነውን አድራሻ/አካውንት ሥራ ለማስጀመር ወደምንችልበት ወደ Activation ቅጽ ለመሔድ ይህንን ማዘዣ መንካት/ክሊክ

2.4 ሥራ የማስጀመሪያ (Activation) ቅጽ

የፈጠርነውን አድራሻ/አካውንት ሥራ ለማስጀመር የግብዣ ኮዶቻችንን (Invite codes) በዚህ ቅጽ በሚገባው ቦታ መጻፍ/ማስገባት አለብን።

ደረጃ 10የግብዣ ኮዶቻችንን (Invite codes) በአስፈላጊ ቦታዎች መጻፍ

ስእል 7፤ ለምሳሌ የቀረበ የተሟላ የሥራ ማስጀመሪያ (Activation) ቅጽ

ደረጃ 11የራይዝአፕ አድራሻ/አካውንት የመፍጠር ሒደቱን ለማጠናቀቅ ይህንን ማዘዣ መንካት/ክሊክ፤ ሒደቱን ማጠናቀቃችንን የሚያበስር መልእክት በስእሉ እንደሚታየው ይገለጣል፤

ስእል 8፤ በተሳካ ሁኔታ አድራሻ መረጠሩን የሚያረጋግጥ መልእክት

ደረጃ 12፦ ወደ ስእል 2 ለመመለስ ይህንን ማዘዣ መንካት/ክሊክ

የምስራች! የራይዝፕ አድራሻ/አካውንት በተሳካ ሁኔታ ፈጥረናል። አሁን ቀደም ሲል ወዳየነው ስእል 2 እንመለሳለን።

ወደ ራይዝአፕ አድራሻችን መግባት (Log in)

በዚህ ገጽ የሚነሱ ርእሰ ጉዳዮች

3.0 ወደ ራይዝአፕ አድራሻችን/አካውንታችን የምንገባው እንዴት ነው?

ወደ ራይዝአፕ አድራሻችን/አካውታችንን ለመግባት የሚከተሉትን ደረጃዎች መከተል አለብን፦

ደረጃ 1የራይዝአፕን ድረ ገጽን ዋና ገጽ (home page) በኤስኤስኤል (SSL) ለመክፈት በዚህ https://mail.riseup.net/ በሔድ

ስእል 1፤ የራይዝአፕ ኢሜይል መግቢያ ገጽ

የራይዝአፕ ኢሜይል ገጽ በሁለት ይከፈላል፤ በስተግራ የኢሜይል መግቢያው () ሲኖር በስተቀኝ ደግሞ News (ዜና) ክፍሉ ይታያል።

ማስታወሻ፦ ከቀረቡት ሁለት የዌብሜይል (webmail) መንገዶች አንዱን መጠቀም እንችላለን። ሆኖም IMP Webmail ከእንግሊዝኛ ውጭ የሚገኙ ቋንቋዎችን ለመጠቀም የበለጠ የተመቸ ነው።

ደረጃ 2Squirrel Webmail ወይም IMP Webmail በሚሉት ክፍሎች User: እና Password: በሚሉት ክፍት ቦታዎች መረጃዎቻችንን ማስገባት/መጻፍ። ሆኖም User: በሚለው ቦታ @riseup.net የሚለውን ፈጽሞ መጨመር የለብንም

አስገዳጅ ያልሆነ ደረጃ፦ በIMP Webmail አገልግሎት Language ከሚለው ስር ከሚከፈተው ቁልቁል ተዘርጊ ምርጫ መካከል የምንጠቀምበትን ቋንቋ መምረጥ እንችላለን።

ደረጃ 3፦ በስእልዩ እንደሚታየው የኢሜይል አድራሻንን/አካውንታችንን ለመክፈት የሚለውን የመግቢያ ማዘዣ መንካት/ክሊክ

ስእል 2፤ የራይዝአፕ ስኵዊርል ዌብሜይል አካውንት

አስገዳጅ ያልሆነ ደረጃ፦ መልእክታችንን ከላቲን ፊደላት ውጪ በሚጠቀም ቋንቋ የምንጽፍ ከሆነ ይህንኑ ለዌብሜይል አካውንቱ ማሳወቅ ይጠቅመናል። ከራስጌ ከሚገኙት አማራጭ የገጽ መግቢያዎች የሚለውን መምረጥ። የስኵዊርል ዌብሜይል (Squirrel Webmail) መስኮት ከታች በሚገኘው ስእል እንደሚታየው ይከፈታል፤

ስእል 3፤ የስኵዊርል ዌብሜይል (Squirrel Webmail) የአማራጮች ገበታ

ደረጃ 4፦ ምርጫዎቹን ሥራ ለማስጀመር ይህን ማዘዣ መምረጥ፤ ከታች እንደሚታየው Options - Display Preferences የሚለው ገበታ ይከፈታል፤

ስእል 4፤ የስኵዊርል ዌብሜይል (Squirrel Webmail) ገበታ Options - Display Preferences ክፍል

ደረጃ 5፦ ወደታች ከተዘረዘሩት ቋንቋዎች መካከል ከላይ በስእል 4 እንደሚታየው የምንፈልገውን መምረጥ፤ ከዚያም ለኢሜይል መልእክቶቻችን የሚስማማውን ፊደል (character) መምረጥ

ይህ አማራጭ የምንልካቸውን እና የምንቀበላቸውን መልእክቶች በትክክል ለመጻፍ/ለማንበብ ያስችላል።

3.1 ቨርቹዋል የትየባ ገበታን (Virtual Keyboard) መጠቀም

ለሕዝብ ክፍት የሆኑ ኮምፒውተሮችን (ለምሳሌ በካፌ፣ በቤተ መጻሕፍት ወዘተ) የምንጠቀም ከሆነ የይለፍ ቃላችንን ለማስገባት ቨርቹዋል የትየባ ገበታን (Virtual Keyboard) መጠቀም እንችላለን። ይህ አሠራር ተጨማሪ የደኅንነት ጥበቃ ይሰጠናል፤ key-logger ከተባሉት አጥፊ ፕሮግራሞች ይጠብቀናል። key-logger የሚባሉት ፕሮግራሞች በመተየቢያ ገበታው የምንጠቀምባቸውን ፊደሎችና ምልክቶች በመከታተል የተጠቃሚ ስሞቻችንን፣ የይለፍ ቃሎችን እና ሌሎችም ጠቃሚ መረጃዎቻችንን ለመሰለለ የሚዘጋጁ ናቸው። ቨርቹዋል የትየባ ገበታዎች (Virtual keyboards) መረጃዎቻችንን (የተጠቃሚ ስም፣ የይለፍ ቃል…) በመተየቢያ ገበታው ፋንታ በማውስ (mouse) እንድንጽፍ ያስችለናል፤ ይህም ለመተየቢያ ገበታ ስለላ እንዳንጋለጥ ያደርገናል።

የራይዝአፕ ቨርቹዋል የትየባ ገበታ ለመጠቀም የሚከተሉተን ደረጃዎች መከተል ነው፤

ደረጃ 1የራይዝአፕ ዋና ገጽ በኤስኤስኤልSSL መክፈት https://mail.riseup.net/

ደረጃ 2የራይዝአፕን የመግቢያ ገጽ ለመከፈት ይህን በሔጃ መንካት/ክሊክ። መግቢያው በስእሉ እንደሚታየው ይከፈታል፤

ስእል 5፤ የራይዝአፕ የመግቢያ ገጽ

ስእል 3፦ ከታች በስእሉ እንደሚታየው ቨርቹዋል የትየባ ገበታውን ለማስጀመር ይህን መንካት/ክሊክ

ስእል 6፤ ቨርቹዋል የትየባ ገበታ

ደረጃ 4፦ ከዚያ ማውሱን በምንፈልገው ፊደልና ምልክት ላይ በማድረግ መንካት/ክሊክ (ወይም ደግሞ የማውስ መጠቆሚያውን በምንፈልገው ፊደል/ምልክት ላይ ለ2 ሰከንድ በማቆየት) የይለፍ ቃላችንንም ሆነ ሌላ መረጃ መጻፍ።

ደረጃ 5፦ ወደ ራይዝአፕ አድራሻችን ለመግባት የሚለውን መንካት/ክሊክ

የአድራሻችንን አሠራር (Settings) መቀየር

በዚህ ገጽ የሚዳሰሱ ጉዳዮች፦

4.0 የአድራሻችንን አሠራር (Settings) መቀየር

ራይዝአፕ አደራሻችን/አካውንታችን የሚሠራባቸውን መንገዶች እንድንቀይር ይፈቅድልናል። የኢሜይል ሳጥናችንን የመያዝ አቅም መወሰን፣ የአድራሻችንን/አካውንታችንን ስም እና አድራሻ መቀየር፣ ሌሎች ነገሮችንም መጨመር እንችላለን። በተጨማሪም ሌሎች ጓደኞቻችንን ወደ ራይዝአፕ ለመጋበዝ የሚያስችሉንን ኮዶች መፍጠር እንችላለን።

ደረጃ 1የራይዝአፕን Account Settings ገጽ በዚህ https://user.riseup.net/ መክፈት

ስእል 1፤ የuser.riseup.net ገጽ

ደረጃ 2፦ የተጠቃሚ ስማችንን እና የይለፍ ቃላችንን በተገቢው ቦታ መጻፍ

ደረጃ 3፦ ይህንን መግቢያ መንካት/ክሊክ፤ ቀጥሎ በስእሉ የሚታየው ገጽ ይከፈታል፤

ስእል 2፤ የriseup.net የተጠቃሚዎች መቆጣጠሪያ ገጽ

4.1 የማይ ሴቲንግ (My Settings) ገጽ

My Settings (ማይ ሴቲንግ) የሚባለው ገጽ ቀደም ሲል በክፍል 2.1 የአድራሻ/አካውንት መረጃ ቅጽ (The Account information form) ያስገባነውን መሠረታዊ መረጃ ያሳየናል።

ደረጃ 1፦ ይህንን የማይሴቲንግ መግቢያ በመንካት/ክሊክ ከታች በስእሉ የሚታየውን ገጽ መክፈት፤

ስእል 3፤ የአሠራር መቀመሪያ (Settings) ገጽ

የተጠቃሚ ስማችንን (user name) እዚህ ገጽ ላይ መቀየር እንችላለን፤ ስማችንን ስንቀይር ግን የኢሜይል አድራሻችንም አብሮ ይቀየራል። የምንመርጠው አዲሱ የተጠቃሚ ስም ከቀድሞው የተለየ መሆን አለበት። እዚህ ገጽ ላይ ሌሎች ነገሮችንም መቀየር እንችላለን ለምሳሌ የይለፍ ቃላችንን፣ አማራጭ የኢሜይል አድራሻችንን እና የመሳሰሉትን በገጹ የሚገኙትን ሁሉ።

ደረጃ 2፦ መለወጥ የምንፈልገውን መረጃ በአዲሱ ከተካን በኋላ ለውጡን ለማጽናት/ለማኖር ይህንን ማዘዣ መንካት/ክሊክ

ስእል 4፤ ያደረግናቸው ለውጦች በትክክል መቀመጣቸውን የሚያረጋግጥ

4.2 የኢሜይል አሠራር መወሰኛ (settings) ገጽ

Email settings ማለትም የኢሜይል አሠራር መወሰኛ ገጽ ከኢሜይል ማስቀመጫ ወይም ማጠራቀሚያው ጋራ የተያያዙ መረጃዎችን እንድንመለከት ወይም እንድንለውጥ የሚያስችለን ክፍል ነው። በራይዝአፕ ላይ ለኢሜይል አድራሻችን የተሰጠውን የማጠራቀሚያ ቦታ መጠን (ኮታ) መምረጥም እንችላለን።

ደረጃ 1፦ ይህንን የክፍሉን መግቢያ ምልክት በመንካት/ክሊክ እዚህ በስእሉ የሚታየውን ገጽ መክፈት፤

ስእል 5፤ የኢሜይል አሠራር መወሰኛ (Email settings) ገጽ

ደረጃ 2Quota በሚለው ክፍት ቦታ ተገቢውን ቁጥር ማስገባት

ማስታወሻ፦ የኢሜይል አድራሻችን የመያዝ አቅም ከ47 ሜጋባይትስ ሊበልጥ አይችልም። ይህ መጠን እጅግ አስፈላጊ ለሆኑ የኢሜይል ግንኙነቶች ይበቃል ተብሎ ይታመናል። ሆኖም ትልልቅ አባሪ ሰነዶችን ወይም ግራፊክ ነገሮችን በብዛት የምንለዋወጥ ከሆነ ራይዝአፕ ጥሩ አማራጭ ላይሆንልን ይችላል።

በዚህ ገጽ ላይ ለአድራሻችን የቅጽል ስሞች (aliases) ልንፈጥረለት ይገባል። ዋናው ስማችን ሳይነካ ሰዎች በእነዚህ የቅጽል አድራሻዎች በመጠቀም ኢሜይል ሊልኩልን ይችላሉ።

ስእል 6፤ የኢሜይል የአሠራር መወሰኛ ገጽ የAliases ክፍል

ምሳሌssayyed@riseup.net ሁለት ቅጽሎች ተፈጥረውለታል። safeandsecure@riseup.net እና salsaytest@riseup.net በሚሉ ቅጽል አድራሻዎች የሚላኩ ኢሜሎች ወደ ዋናው/የመጀመሪያው አድራሻው ያመራሉ። ዋናውን አድራሻችንን እንዳይታወቅ ለማድረግ ከፈለግን የቅጽል ስም/አድራሻ አማራጭ በጣም ጠቃሚ ነው።

ደረጃ 4፦ የፈጠርናቸውን ቅጽል ስሞች ለማኖር ይህን ማዘዣ መንካት/ክሊክ

4.3 የመጋበዣ (Invites) ገጽ

Invites የተባለው ገጽ የግብዣ ኮዶችን (invite codes) የምንፈጥርበት ነው። ጓደኞቻችን እና የሥራ ባልደረቦቻችን ራይዝአፕን እንዲቀላቀሉ ለማስቻል እነዚህ ኮዶች ያስፈልጉናል።

ማስታወሻ፦ እያንዳንዱ አዲስ የራይዝአፕ ተጠቃሚ ለመሆን የሚፈልግ ሰው ከሁለት የተለያዩ ተጠቃሚዎች የግብዣ ኮድ () ማግኘት አለበት። ተጠቃሚዎች የፈለጉትን ያህል የግብዣ ኮዶችን መፍጠር ይችላሉ።

ደረጃ 1፦ ይህን የገጹን ምልክት በመንካት/ክሊክ በስእሉ የሚታየውን መክፈት፤

ስእል 7፤ የ Invites ገጽ

ደረጃ 2፦ ከታች በስእሉ እንደሚታየው የግብዣ ኮዶችን ለማዘጋጀት ይህንን ማዘዣ መንካት/ክሊክ

ስእል 8፤ አዲስ የተፈጠሩ የግብዣ ኮዶች ምሳሌ

ማስታወሻ፦ እያንዳንዱ የግብዣ ኮድ የሚሠራው ለአንድ ወር ብቻ ነው። ይህ ጊዜ ካለፈ በኋላ ኮዶ አያገለግልም።

ደረጃ 3፦ የግብዣ ኮዱን አትሞ ለማውጣትና የራይዝአፕ ኢሜይል አካውንት እንዲኖረው ለተመኘንለት ሰው ለመስጠት ይህን ማተሚያ Print invites መንካት/ክሊክ

ደረጃ 4፦ ከተጠቃሚዎች ማዘዣ ለመውጣት ይህንን መንካት/ክሊክ

የሚዘወተሩ ጥያቄዎች እና ክለሳ

5.0 የሚዘወተሩ ጥያቄዎች

ደበበ እና ቀነኒ ራይዝአፕ ለአጠቃቀም ምቹ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ለማኅበራዊ እሴቶች የሚሰጠው ቦታ አስደስቷቸዋል። ሆኖም ጥቂት የሚረብሿቸው ጥያቄዎችም አሉ። እንደመታደል ሆኖ ባልደረባቸው መሃሪ ጥያቄዎቻቸውን ሊመልስላቸው ይችላል።

*ጥያቄIMP webmail እና Squirrelmailን የምንጠቀምባቸው የተለያዩ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?*

*መልስ፦ በመሠረቱ በሁለቱ መካከል ይህ ነው የሚባል ልዩነት የለም። አንደኛው በተለያየ ምክንያት፣ ለምሳሌ ለጥገኛ ወይም ለሙከራ፣ አገልግሎት መስጠት ቢያቆም ወደሌላው በመሔድ አገልግሎቱን ማግኘት እንችላለን። IMP webmail ከእንግሊዝኛ ውጭ ላሉ በርካታ ቋንቋዎችም የሚሠራ መሆኑ ግን የሚጠቀስ ነው።*

*ጥያቄ፦ የራይዝአፕ አድራሻ/አካውንት ስፈጥር ስለራሴ ምንም መረጃ እንዳልተጠየኩ አስተውያለሁ።*

*መልስ፦ ትክክል ብለሃል፤ ስለራስህ መረጃ እንድትሰጥ አትጠየቅም። ለማንኛውም ከ3-6 ወር ባለው የጊዜ ክፍተት የይለፍ ቃላችንን መቀየር እንዳለብን መርሳት የለብንም።*

*ጥያቄ፦ እኔና ደበበ የራይዝአፕ የኢሜይል አድራሽ/አካውንት ባለቤቶች ሆነናል። አንተም እንዲኖርህ ለማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?*

*መልስ፦ ሁለታችሁም የግብዣ ኮድ አውጥታችሁ ልትልኩልኝ ይገባል። ከዚያ የላካችሁልኝን የግብዣ ኮድ በመጠቀም የራይዝአፕ አድራሻውን እከፍትበታለሁ።*

ማስታወሻራይዝአፕ በበጎ አድራጊዎች ስጦታ እና በበጎ ፈቃደኞች ጥረት ለትርፍ ከሚንቀሳቀሱ የኢሜይል አገልግሎት ሰጪዎች ጋራ እየተወዳደር የሚሠራ እንደመሆኑ ተግዳሮቶቹ ብዙ ናቸው። ራይዝአፕ ክራብግራስ (Crabgrass) የተባለ የራሱን ፌስቡክ አከል አማራጭ አቅርቧል። ይህም ከፌስቡክ ሌላ ተጨማአሪ አማራጭ መሆን የሚችልና መሠረታዊ መዋቅሩም ድብቅ ያልሆነ (open source) ነው። ክራብግራስ (Crabgrass) በጣም የተሻለ የምሥጢራዊነት እና የደኅንነት ጥበቃ ያለው ሲሆን በዋናነት የማኅበረሰብ አገልግሎት ሰጪዎች ወይም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም አካባቢ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች እንዲጠቀሙበት ታስቦ የተሰራ ነው። ራይዝአፕ ከዚህም ሌላ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ተወዳዳሪ ወይም የኢሜይል አገልግሎት አብዮት ሊፈጥሩ የሚችሉ አገልግሎቶችን ለመጀመር ያስባል።

 • Collaborative Document Editing (etherpad)፦ ይህ አገልግሎት የተለያዩ ተጠቃሚዎች አንድን ዶክመንት በተመሳሳይ ጊዜ እንዲያርሙ ወይም የአርትኦት ስራ (edit) እንዲያደርጉ የሚያስችላቸው ነው። አገልግሎቱን የጋርዮሽ አርትኦት ልንለው እንችላለን።

 • Encrypted Internet Proxy (openvpn)፦ ይህ አገልግሎት ከቶር (Tor) ጋራ ተመሳሳይነት ባለው ኢንክሪፕት የተደረገ የፕሮክሲ ሰርቨር ኢንተርኔት ለመጠቀም የሚያስችለን ነው።

 • Real-Time Chat (XMPP)፦ ይህ አገልግሎት በቀጥታ ቻት ለማድረግ የሚያስችል ነው። ከጂሜይል (Gmail) ቻት እና ማይክሮሶፍት ኢንስታንት ሜሴጂንግ (Microsoft Instant Messaging) ጋራ ተመሳሳይ ነው።

5.1 የክለሳ ጥያቄዎች

 • ኢሜይላችንን በዌብሜይል ወይም በኢሜይል ፕሮግራም ማንበብ ልዩነቱ ምንድን ነው?

 • Secure Socket Layer (SSL) ምንድን ነው፣ የሚሠራውስ እንዴት ነው?

 • ቨርቹዋል የትየባ ገበታ (virtual keyboard) ምንድን ነው፣ የሚሠራውስ እንዴት ነው?

 • ለኢሜይላችን “alias” ወይም ቅጽል ስም/አድራሻ መፍጠር የምንችለው እንዴት ነው?

 • አዲስ የተፈጠረ የግብዣ ኮድ አገልግሎት ሊሰጥ የሚችለው ለስንት ጊዜ ነው?