9. በማኅበራዊ ገጾች የራስን እና የመረጃዎችን ደኅንነት መጠበቅ

Updated2013

መመሪያው በወቅቱ አልተሻሻለም፤ በቅርቡ ይሰረዛል

ኦንላይን ቡድኖች/ስብስቦች (communities) ኢንተርኔት ከተፈጠረ ጀምሮ አብረው የቆዩ ናቸው። መጀመሪያ የአጀንዳ መድረኮች (bulletin boards) እና የኢሜይል አድራሻዎችና ግንኙነቶች መዝገብ (email lists) በስፋት ይታወቁ ነበር። እነዚህ አባሎቻቸው እንዲገናኙ እና በተመረጡ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ሐሳብ እንዲለዋወጡ የሚያስችል ነው። ዛሬ ግን ማኅበራዊ ገጾች (social networking websites) ሰዎች ሊያደርጉ የሚችሉትን ግንኙነት አይነትና መጠን በእጅጉ አስፋፍተውታል። የማኅበራዊ ገጾቹ ተጠቃሚዎች መልእክቶችን፣ ምስሎችን፣ ፋይሎችን መለዋወጥ ይችላሉ፤ በእያንዳንዱን ቅጽበት የደረሱበትን ወይም የገጠማቸውን በየሰከንዱ መለዋወጥም ይችላሉ። በእርግጥ እነዚህ አገልግሎቶች በማኅበራዊ ገጾች ብቻ የሚገኙ አይደሉም፤ በሌሎች የኢንተርኔት መስኮችም መረጃዎችን መለዋወጥ ይቻላል።

እነዚህ የማኅበራዊ ግንኙነት መረቦች ኦንላይንም ይሁን ከኦንላይን ውጪ (online and offline) የሚደረጉ ማኅበራዊ መስተጋብሮችን ስለሚያቀላጥፉ ጠቃሚ ናቸው። ይሁንና እነዚህን መረቦች ስንጠቀም ስለራሳችን የምንገልጻቸው መረጃዎች በሌሎች ወገኖች ለሌላ ዓላማ ሊውሉ ይችላሉ። የማኅበራዊ ግንኙነት ገጾችን እንደ አንድ ትልቅ ድግስ ወይም ፓርቲ ልንቆጥረው እንችላለን። በእንዲህ አይነቱ ቦታ የምናውቃቸውም የማናውቃቸውም ሰዎች ይገኛሉ። በዚህ ቦታ ብዙ በየደቂቃው የምናደርጋቸው ነገሮች ጨምሮ ግላዊ መረጃዎቻችን በጀርባችን ላይ በግልጽ ተጽፈው በታዳሚዎቹ መካከል እንደማለፍ ነው። ይህንን መረጃ እኛ ሳናውቀው የተሰበሰበው ታዳሚ ሁሉ ያየዋል ማለት ነው:: ሁሉንም መረጃዎቻችንን ሁሉም ሰው እንዲያውቅ እንፈልጋለን?

የማኅበራዊ ግንኙነት መረቦች በግል የንግድ ኩባንያዎች ባለቤትነት የተያዙ መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም። እነዚህ ኩባንያዎች ትርፍ የሚያገኙት የተጠቃሚዎችን መረጃ በመሰብሰብ እና በተለይም ለአስተዋዋቂዎች በመሸጥ ነው። ወደ አንድ የማኅበራዊ ግንኙነት መረብ/ገጽ ስንገባ ኢንተርኔት ከሚሰጠን የነጻነት ቀጣና ወጥተን በመረቡ/ገጹ ባለቤቶች ሕግና አስተዳደር ብቻ ወደሚመራ ስፍራ እየገባን ነው። በእነዚህ መረቦች/ገጾች የደኅንነት ምርጫ (Privacy settings) ምሥጢራችንን የሚጠብቅልን ከሌሎች የመረቡ አባላት እንጂ ከመረቡ ባለቤቶች አይደለም። በመሠረቱ መረቦቹን ስንቀላቀል መረጃዎቻችንን ሁሉ ለመረቡ/ገጹ ባለቤቶች በእምነት ሰጥተናቸዋል።

ስሱ መረጃዎች እና ጉዳዮች እያሉን ማኅበራዊ መረቦቹን ለመጠቀም ከፈለግን፣ ተያይዘው የሚመጡ የምሥጢራዊነት እና የደኅንነት ጉዳዮችን በጥብቅ ልናስብበት ይገባል። በተለይም የሰብአዊ መብት አቀንቃኞች በማኅበራዊ ገጾች እጅግ ተጋላጭ ሆነው ይታያሉ። ስለዚህም በገጾቹ ላይ ስለራሳቸውም ሆነ አብረዋቸው ስለሚሠሩት ሰዎች ስለሚገልጹት መረጃ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል። የማኅበራዊ ግንኙነት መረቦችን መጠቀም ከመጀመራችን በፊት መረጃዎቻችን ምን ያህል ሊያጋልጡ እንደሚችሉ ማሰብ፣ ራሳችንን እና አብረውን የሚሠሩ ሰዎችን ለመጠበቅ የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ አለብን። ይህ ምእራፍ በማኅበራዊ መረቦች/ገጾችን መጠቀም ጋራ ተያይዘው የሚመጡ የደኅንነት ስጋቶችን እንድንረዳ ያግዘናል።

አስረጅ አጋጣሚ

:Snippet

ማኅበራዊ መረቦችን/ገጾችን መጠቀም እንድናቆም አንመከረም። ሆኖም ራሳችንንም ሆነ ጓደኞቻችንን ከአደጋ ለመጠበቅ ተገቢውን የደኅንነት ቅድመ ጥንቃቄ እየወሰድን መጠቀም ይኖርብናል።

የምእራፉ ዋና ዋና ጭብጦች

 • የማኅበራዊ ግንኙነት መረቦች/ገጾች ሳናስበው ስሱ መረጃዎችን ሊያጋልጡብን የሚችሉት እንዴት ነው?
 • በማኅበራዊ ግንኙነት መረቦች/ገጾች የራሳችንን እና የሌሎችንም ደኅንነት እንዴት መጠበቅ ይቻላል?

የማኅበራዊ ገጾች አጠቃቀም ጥቆማዎች

 • ሁል ጊዜ ሊጠየቁ የሚገባቸው ጥያቄዎች፡
  -  ኦንላይን የምናሰፍረውን መረጃ ሊያገኙ የሚችሉት እነማን ናቸው?
  - በማኅበራዊ ግንኙነት ገጾች ላይ የምናሰፍራቸውን መረጃዎች የሚቆጣጠረውና በባለቤትነት የሚይዘው ማን ነው?
  - ሌሎች ስለእኛ የሚጽፉት/የሚሰጡት መረጃ ምንድን ነው?
  - ጓደኞቼ ስለእነርሱ ያለኝን መረጃ ለሌሎች ባጋራ ይፈቅዳሉ?
  - በገጾቹ የምናገኛቸው ሰዎች ሁሉ የሚታመኑ ናቸው?
 • ምንጊዜም ወደ ማኅበራዊ ገጾች የምንገባበት የይለፍ ቃል አስተማማኝ መሆኑን ማረጋገጥ አለብን። ይህ ካልሆነ ግን የይለፍ ቃላችንን በግምት ወይም በስርቆት ማግኘት የቻለ ሰው ወደ አድራሻችን በመግባት ስለራሳችን እና ስለሌሎችም ያሉንን በርካታ መረጃዎች ሊወስድብን ይችላል። የይለፍ ቃሉን በየጊዜው በቋሚነት የመቀየር ልማድ ሊኖረን ያገባል። ለተጨማሪ ማስታወሻ ምእራፍ 3ን. አስተማማኝ (የምሥጢር) የይለፍ ቃል መፍጠር እና መጠቀም መመልከት ነው።

 • ማኅበራዊ መረቦች/ገጾች የሚሰጡትን የተለመደ የደኅንነት አማራጮች (privacy settings) አጠቃቀም መረዳት እና እንዴት መቀየር እንደሚቻል ማወቅ፤

 • ለተለያዩ ሥራዎች እና ዘመቻዎች/ቅስቀሳዎች የተለያዩ አድራሻዎችን/ስሞችን (separate accounts/identities) መጠቀም የተመረጠ ነው። የማኅበራዊ መረቦች ደኅንነት ቁልፍ በአባሎቹ መካከል ያለው መተማመን ነው። የተለያዩ አድራሻዎችን መጠቀም ይህን መተማመን ለመፍጠር አንድ አማራጭ ነው።

 • ለሕዝብ ክፍት ከሆኑ የኢንተርኔት መገልገያ ቦታዎች የማኅበራዊ መረቦች/ገጾች አድራሻችንን ስንከፍት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። ሕዝብ የሚያገለገልባቸውን ኮምፒውተሮች ስንጠቀም የይለፍ ቃሉን እና የሐሰሳ ታሪኩን (browsing history) ከማሰሻው (browser) መደምሰስ ያስፈልጋል። ምእራፍ 6. ስሱ መረጃዎችን በጥንቃቄ ማጥፋት የሚቻለው እንዴት ነው? በድጋሚ መመልከት ይቻላል።

 • የተጠቃሚ ስማችንን፣ የይለፍ ቃሎችን እና ሌሎችንም የተለጠፉ መረጃዎች ደኅንነት ለመጠበቅ ማኅበራዊ ገጾችን በhttps:// ብቻ መክፈት ፈጽሞ ሊዘነጋ የማይገባው ነው። ከ“http://” ይልቅ “https://”ን መጠቀም ከማሰሻችን ወደ ማኅበራዊ ገጹ መካከል የሚኖረው ትራፊክ ተጨማሪ ከለላ እንዲያገኝ ያደርጋል። ለተጨማሪ ማብራሪያ ምእራፍ 8. ማንነትን መደበቅ እና የኢንተርኔት ሳንሱርን/እገዳን ማለፍ መመልከት።

 • የደረስንበት ማስታወሻ/ዘገባ (status updates) በየጊዜው በማኅበራዊ ገጾች ላይ ከሚገባው በላይ ስለእኛ የሚገልጽ መረጃ እንዳንለጥፍ መጠንቀቅ አስፈላጊ ነው። በመረባችን ውስጥ ያሉትን ጓደኞቻችንን ብናምናቸው እንኳን፣ ሌሎች የማናውቃቸው ሰዎች በቀላሉ መልእክቶቹን ማግኘት ይችላሉ።

 • ብዙዎቹ የማኅበራዊ ግንኙነት መረቦች/ገጾች መረጃዎቻችንን ከሌሎች ማኅበራዊ መረቦች ጋራ እንድናቀናጅ ይፈቅዳሉ። ለምሳሌ በትዊተር ላይ የለጠፍነው/የጻፍነው ነገር ወዲያውኑ በፌስቡክ ገጻችን ላይ ሊነበብ/ሊለጠፍ ይችላል። የማኅበራዊ ገጾች አድራሻዎቻችንን ስናቀናጅ መጠንቀቅ ይኖርብናል! ምክንያቱም በአንዱ ላይ የደበቅነው ማንነታችን በሌላው አድራሻ የተነሣ ሊጋለጥ ይችላልና ነው።

 • በማኅበራዊ መረቦች/ገጾች ላይ የምናሰፍረው መረጃ ይዘት ለአደጋ እንዳይጋለጥ በንቃት መመልከት አለብን። የማኅበራዊ ግንኙነት ድረ ገጾች ስሱ መረጃዎችን ለማስቀመጥ ቀዳሚ ምርጫችን ሊሆኑ አይገባም! መንግሥታት ማኅበራዊ ገጾች በቀላሉ በድንበራቸው ውስጥ እንዳይታዩ ማድረግ ይቻላሉ፤ በገጾቹ ላይ የሚገኙ ይዘቶች “ተቀባይነት የሌላቸው” (objectionable) ከመሰሉዋቸው ይህን ከማድረግ አይመለሱ ይሆናል። የድረ ገጾቹ አስተዳዳሪዎችም እንዲሁ ገጻቸው በአገሩ ውስጥ ሳንሱር እንዳይደረግባቸው ሲሉ “አስደንጋጭ/አሳሳቢ” የሚሉትን ይዘት ከገጹ ሊያነሱት ይችላሉ።

ግላዊ መረጃዎችን መለጠፍ/መግለጽ

የማኅበራዊ መስተጋብር መረቦች/ገጾች ሌሎች ሰዎች በቀላሉ ፈልገው እንዲያገኙን ለመርዳት ሲሉ ስለራሳችን ብዙ ግላዊ መረጃዎችን እንድንሰጣቸው ይጠይቁናል። ይህ አሠራር በተጠቃሚዎቹ ላይ የሚፈጥረው ትልቁ አደጋ በሐሰት እኛን መስለው “እገሌ ነኝ” ብለው መቅረብ ለሚፈልጉ “የማንነት አጭበርባሪዎች” (identity fraud) የሚያጋልጠን መሆኑ ነው። “እገሌ ነኝ” ብሎ መቅረብና ወንጀል መፈጸም እየተለመደ መጥቷል። (ይህ ማንነትን መጭበርበር፣ ራስን ከክትትል ለመሰወር ከሚፈጠረው ማንነትን ከመሰወር ጋር የተለየ መሆኑን ያጤኗል!) በተጨማሪም፣ ስለራሳችን ብዙ መረጃ በሰጠን መጠን፣ ሊከታተሉን እና ለጎዱን ወይም ሥራችንን መቆጣጠር ለሚፈልጉ የመንግሥት አካላት ጠቃሚ መረጃ እየሰጠናቸው ነው። በውጭ አገር የሚገኙ አቀንቃኞች/ቀስቃሾች (activists) በኢንተርኔት በሚሰጡዋቸው ያልታሰበባቸው መረጃዎች አገር ቤት የሚገኙ ቤተሰቦቻቸው እና ሌሎች ሰዎች በክትትል ስር እንዲወድቁ ሊያደርጉ ይችላሉ።

ራሳችንን እንጠይቅ፡ የሚከተሉትን መረጃዎች መለጠፍ/መግለጽ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

 • የልደት ቀን
 • የስልክ ቁጥር
 • አድራሻ
 • የቤተሰብ አባሎቻችን ማንነት
 • የጾታ ፍላጎት (ምርጫ)
 • የትምህርት እና የሥራ ታሪካችን

:Snippet

ጓደኞች፣ ተከታዮች እና የምናውቃቸው ሰዎች

ወደ ማንኛውም የማኅበራዊ መስተጋብር አፕሊክሼን ስንገባ ስለማንነታችን ግላዊ መረጃዎችን ከሰጠን በኋላ ቀጥሎ የሚቀርብልን ጥያቄ ከሌሎች ጋራ ግንኙነት፣ ጓደኝነት እንድንመሠርት ነው። እነዚህ የምናገኛቸው ሰዎች ከዚያ ቀደም የምናውቃቸው እና የምናምናቸው እንደሆኑ ይታሰባል፤ ነገር ግን ከዚያ ቀደም ፈጽሞ የማናውቃቸው ነገር ግን ከእኛ ጋር የሚቀራረብ ፍላጎት/አመለካከት ያላቸው ሰዎች የተሰባሰቡበትን የኦንላይ ስብስብ ልንቀላቀልም እንችላለን። ትልቁ ነገር ለዚህ የኦንላይን ስብስብ የምናካፍለው መረጃ ምን እንደሆነ ማወቅና መጠንቀቅ ነው። ፌስቡክን የመሳሰሉ የማኅበራዊ መስተጋብር ገጾችን ስንጠቀም፣ በዚያ የምናስቀምጠውን መረጃ ለሌላ አላማ እንዳያውሉብን ከምናውቃቸውና ከምናምናቸው ሰዎች ጋራ ብቻ ግንኙነት/ጓደኝነት መጀመር የሚመረጥ ነው።

:Snippet

የደረስኩበት/ የሁኔታ ማሳወቂያ (Status updates)

በትዊተር፣ በፌስቡክ እና በመሰል ገጾች፣ በሁኔታ ማስታወቂያ (Status updates) የሚጻፉት ነገሮች የሚከተሉትን ጥያቄዎች የሚመልስ ነው፤ አሁን ምን እየሠራሁ ነው? ምን እየሆነ ነው (ከምሰማው፣ ከማየው፣ ከማነበው)? ስለ “ሁኔታ ማሳወቂያ”መረዳት ያለብን በጣም አስፈላጊው ጥያቄ የምንጽፈውን የሚያየው/የሚከታተለው ማነው የሚለው ነው። በተለምዶ የሚሠራው የ“ሁኔታ ማሳወቂያ” አማራጭ ማንም በኢንተርኔት ላይ ያለ ሰው የምንለጥፈውን ነገር እንዲመለከት የሚፈቅድ ነው። የምንለጥፈውን ነገር ጓደኞቻችን ብቻ እንዲመለከቱት እና ከሌሎች የተደበቀ እንዲሆን ከፈለግን ማኅበራዊ ገጹ ይህን እንዲያደርግልን ማዘዝ ይሆርብናል።

በትዊተር ይህን ለማድረግ “ትዊቶቼ ይጠበቁልኝ” (“Protect Your Tweets”) የሚለውን ማግኘትና ማስተካከል ነው። በፌስቡክ ደግሞ የደኅንነት አማራጮችን ወደሚሰጠው ክፍል በመሔድ “ጓደኞቻችን ብቻ” (“Friends Only”) የሚለውን መምረጥ ነው። እንደዚህም ቢሆን ከጓደኞቻችን አንዱ የእኛን መልእክት መልሶ ሊለጥፈውና ጓደኛችን ያልሆነ ሰው ሊያየው ይችላል። የሚቻል ከሆነ በማኅበራዊ ገጾች ከምናገኛቸው ጓደኞቻችን ጋራ ለሌሎች ስለምናካፍለው ወይም መልሰን ስለምንለጥፈው መረጃ የጋራ መግባባት መፍጠር ይጠቅማል። ጓደኞቻችን ሌላ ሰው እንዲያውቀው የማይፈልጉት ነገር ካለና ይህን ለእኛ አካፍለውን ከሆነ፣ ይህን መረጃ አሳልፈን እንዳንሰጥ መጠንቀቅ ይኖርብናል። በዚህ ጉዳይ ስጉና ጠንቃቃ መሆን፣ ሌሎችም እንዲሁ እንዲሆኑ መጠየቅ ይገባል።

በ“ሁኔታ ማሳወቂያ” የተጻፈ ነገር ሰዎችን ለማጥቃት ወይም ለመወንጀል ጥቅም ላይ የዋለባቸው አጋጣሚዎች ሞልተዋል። በአሜሪካ ስለተማሪዎቻቸው የሚሰማቸውን ስሜት የለጠፉ/ፖስት ያደረጉ መምህራን ከሥራቸው ተባረዋል፤ ስለቀጣሪዎቻቸው የጻፉም ሥራቸውን ያጡበት አጋጣሚ አለ። ስለምንለጥፋቸው ነገሮች ሁለት ጊዜ ማሰብ አይከፋም።

የኢንተርኔት ይዘቶችን ማጋራት

ጓደኞቻችን እንዲመለከቱት የምንሻውን ድረ ገጽ “ሊንክ” (link) ማድረግ የተለመደ ነው። ነገር ግን “እነዚህን ሊንኮች የሚከታተሉት እነማን ናቸው፣ ምንስ አይነት ምላሽ ይኖራቸዋል?” ብሎ መጠየቅ ይገባል። ለምሳሌ ሊንክ ያደረግነው ድረ ገጽ በአገራችን ያለውን ጨቋኝ መንግሥት ስለማውረድ የሚያትት ሊሆን ይችላል፤ ይህ የአገዛዙን ትኩረት ሊስብ ይችላል።

ለሌሎች ያካፈልናቸውን ወይም ትኩረታችንን ስለሳቡ ጓደኞቻችን ብቻ እንዲመለከቷቸው የምንፈልጋቸው ነገሮች ሲገጥሙን የደኅንነት አማራጫችንን (privacy settings) ማስተካከል መርሳት የለብንም።

ያለንበትን ቦታ ማስታወቅ

መረጃውን ከሰጠናቸው ብዙዎቹ የማኅበራዊ ግንኙነት ድረ ገጾች ያለንበትን ቦታ ይገልጣሉ። ጂፒኤስ (GPS) በተገጠመላቸው ተንቀሳቃሽ ስልኮች ማኅበራዊ ገጾችን ከጎበኘን ያለንበትን ቦታ በቀጥታ ያሳያሉ። ይህ ማለት ግን ከሞባይል ውጪ ገጾቹን ስንጎበኝ ያለንበት ቦታ ሊታወቅ አይችልም ማለት አይደለም። ኮምፒውተራችን ከኢንተርኔት የሚገናኝበት መረብ አድራሻውን (ያለበትን ቦታ) የሚገልጽ ሊሆን ይችላል። ለዚህ መፍትሔው የደኅንነት አማራጮቻችንን ማስተካከል ነው።
ለሌሎች በምናካፍላቸው ፎቶዎች እና ቪዲዮ ላይ ያለውን የቦታ ማሳያ ምርጫ (location settings) በጥንቃቄ ማስተካከል ይኖርብናል። ፎቶዎች እና ቪዲዮዎች ያለንበትን አይገልጹም ብለን አንዘናጋ፤ ይልቅ እርግጠኛ ለመሆን የደኅንነት ምርጫችንን ደጋግመን እናረጋግጥ። በኤልክትሮኒክ ፍሮንቲር ፋውንዴሽን ድረ ገጽ ስለ ቦታ ስወራ እና መረጃውን እስከመጨረሻ እንዳይጠፋ ስለማድረግ ተጨማሪ ማብራሪያ መግኘት እንችላለን።

ቪዲዮዎችን/ፎቶዎችን ማጋራት

ፎቶዎች እና ቪዲዮዎች የሰዎችን ማንነት በቀላሉ ሊገልጡ ይችላሉ። ስለዚህም ፎቶዎችን እና ቪዲዮዎችን ስንለጥፍ ምስላቸው በእነርሱ ውስጥ ያሉ ሰዎችን ፈቃድ/ስምምነት ማግኘት ይኖርብናል። የሌላ ሰው ምስል ስንለጥፍ የእርሱን ደኅንነት ለአደጋ ልናጋልጥ እንደምንችል መዘንጋት የለብንም። ምንግዜም የሰዎቹን ይሁንታ ሳናገኝ ምስላቸውን የሚያሳይ ፎቶም ይሁን ቪዲዮ መለጠፍ የለብንም። ፎቶዎች እና ቪዲዮዎች ሳናውቀው ሌሎችንም በርካታ መረጃዎችን ሊገልጡብን ይችላሉ። ለምሳሌ ብዙዎቹ ካሜራዎች ፎቶ የተነሳበትን ቀን፣ ሰዓትና ቦታ፣ የካሜራውን እና የፎቶውን አይነት ጭምር በስውር የሚመዘግብ አሠራር (metadata tags) አላቸው። ፎቶ እና ቪዲዮ ለማካፈል የሚያስችሉ ድረ ገጾች ይህን መረጃ ከለጠፍነው ፎቶ ወይም ቪዲዮ ጋራ ሊያትሙት ይችላሉ።

:Snippet

ፈጣን ምልልሶች/ቻት (Instant chats)

ብዙዎቹ የማኅበራዊ ግንኙነት ድረ ገጾች ከጓደኞቻችን ጋራ (ልክ በድምፅ በቀጥታ እንደምናወራው ሁሉ) በጽሑፍ በቀጥታ እንድንመላለስ የሚያስችል አገልግሎት አላቸው። አሠራሩ ከፈጣን መልእክት (Instant Messaging) ጋራ ተመሳሳይ ነው፤ በኢንተርኔት መረጃ ለመለዋወጥም ፈጽሞ የማያስተማምን መንገድ ነው። ፈጣን ምልልሶቻችን (ቻቶቻችን) ደኅንነታቸው የሚያስተማምን እንዲሆንልን ከፈለግን የቻቱ ተካፋዮች በሙሉ ወደማኅበራዊ ገጹ በ https:// በኩል መግባት አለብን። ይህ ካልሆነ ደግሞ ፒድጂን (Pidgin) መጠቀም ይኖርብናል፤ ፒድጂን ታሪክ እንዳይመዘግብ ካዘዝነው ግንኙነታችን ኢንክሪፕትድ ስለሚሆን ደኅንነታችን ተጠብቋል ማለት ነው። (ለተጨማሪ መረጃ የፒድጂንን የአጠቃቀም መመሪያ ('Pidgin – secure instant messaging' hands-on guide) ማንበብ ነው።)

ቡድኖችን (groups)፣ ዝግጅቶችን ( events) እና ማኅበረሰቦችን (communities) መፍጠር/መቀላቀል

ለመሆኑ አንድን የኢንተርኔት ላይ ቡድን ወይም ማኅበረሰብ ስንቀላቀል ምን መረጃ እየሰጠን ይሆን? እነዚህን ስብስቦች መቀላቀል ማለት ምን ማለት ነው? ሰዎች እኛ ወደፈጠርነው አንድ ስብስብ ሲቀላቀሉ ለዓለም እያስታወቁ ያሉት ምንድን ነው? በዚህ መንገድ ሳናውቀው ሰዎችን ለአደጋ እናጋልጥ ይሆን?

አንድን የኦንላይን ቡድን ወይም ማኅበረሰብ ስንቀላቀል ስለራሳችን ለሌሎች የምንገልጸው ነገር አለ። በደፈናው ሰዎች የተቀላቀልነው ቡድን ወይም ማኅበረሰብ የሚለውን ወይም የሚሠራውን እንደምንደግፈው አድርገው ይረዱታል፤ ይህ የማያስፈልግ ትኩረ ሊስብብን ወይም አደጋ ሊጋብዝብን የሚችል መሆን አለመሆኑን መመዘን አለብን። የምንቀላቀለው ቡድን የማናውቃቸው በጣም ብዙ አባላት ያሉት ከሆነ አካውንታችንን/አድራሻችንን ለመጠበቅ የመረጥነው የደኅንነት ቀመር ለአደጋ የሚጋለጥበት ሁኔታ ሊፈጠር የሚችልበት እድል ይጨምራል። ስለዚህ ቡድኖቹን ከመቀላቀላችን በፊት የምንገልጠውን እና የምንደብቀውን መረጃ ልናስብበት የተገባ ነው። ለምሳሌ የማናውቃቸው ሰዎች ጭምር እንዲለዩን እውነተኛ ስማችንን እና ፎቶዋችንን እንጠቀማለን?

በተመሳሳይ ቡድኑን የፈጠርነው እኛ ነን እንበል። ሌሎች ወደዚህ ቡድናችን ሲቀላቀሉ ለቀሪው ዓለም ምን እያሉ ነው? ለምሳሌ የፈጠርነው ቡድን የሚያቀነቅነው ሐሳብ የጥቂቶችን መብት ከመጠበቅ ጋራ የተያያዘ ሊሆን ይችላል። ሰዎች ይህን ቡድን ሲቀላቀሉ ያላሰቡት አደጋ ሊመጣባቸው ይችል ይሆን?

:Snippet

ማኅበራዊ መረቦች/ገጾች

ፌስቡክ (Facebook)##

ፌስቡክ በዓለማችን ትልቁ የማኅበራዊ ግንኙነት ድረ ገጽ ነው። በማኅበራዊ መረቦች ሰዎችን ለማግኘት የሚፈለጉ በቅድሚያ ከሚሔዱባቸው ቦታዎች ቀዳሚው ፌስቡክ ነው። ይህ ማለት ፌስቡክን መጠቀም ሌሎች ገጾችን ከመጠቀም የበለጠ ለአደጋ የተጋለጠ ነው እንደማለት ነው። በመላው ዓለም ተጠቃሚዎች ያሉት በመሆኑ የምንለጥፈውን ነገር ማንም ሊያየው ይችላል ማለት ነው።

የፌስቡክ መሥራች ማርክ ዙከርበርግ ራሱ “የኦንላይን ምሥጢራዊ ደኅንነት አብቅቶለታል” ሲል በአደባባይ ተናግሯል፤ ስለዚህም በፌስቡክ ምሥጢራዊነትንና ደኅንነትን ማረጋገጥ እጅግ አጠራጣሪ ነው። አደናጋሪውን የፌስቡክ የምሥጢራዊነት አማራጭ በመጠቀም መረጃዎቻችንን የመረጥናቸው “ጓደኞቻችን” ብቻ እንዲያዩት አዘን/አድርገን ይሆናል፤ ሆኖም “ጓደኞቻችን” ያልሆኑ ሰዎች በቀላሉ በኢንተርኔት ሐሰሳ በመጠቀም የተወሰነ መረጃ ማየት ይችላሉ። የጨዋታዎች እና የተለያዩ አፕሊኬሽኖች ፈጣሪዎች (developers) መረጃዎቻችንን በቀላሉ ሊያገኙት ይችላሉ።

አንድ አስገራሚ ነገር መርሳት የለብንም፤ አንድ ጊዜ የፌስቡክ አካውንት/አድራሻ ከፈጠርን በኋላ ልናጠፋው አንችልም። ጥያቄውን ካቀረብን ፌስቡክ አካውንታችንን “ከአገልግሎት ውጪ” ('deactivate') ሊያደርገው ይችላል፤ ሆኖም አንድም መረጃው ሳይጠፋና ሳይነካ መልሰን ወደ አገልግሎት ልናመጣው ('reactivate') እንችላለን። መረጃችን ከፌስቡክ ፈጽሞ አይጠፋም።

በhttp://www.facebook.com/terms.php የምናነበው “ስምምነት” ነገሩን የበለጠ ግልጽ ያደርገዋል- “በአእምሯዊ የፈጠራ ባለቤትነት መብት ሽፋን የተሰጣቸውን ፎቶዎች እና ቪዲዮዎች ('IP content') በተመለከተ እርስዎ (ተጠቃሚው) የሚከተሉትን ፈቃዶች ሰጥትውናል፤ ይህም በእርስዎ የምሥጢራዊነት (privacy) እና የአፕሊኬሽን ምርጫዎች (application settings) ላይ የተመሠረት ይሆናል። በዚህም በፌስቡክ የሚለጥፏቸውን ማናቸውንም ይዘቶች ያለገደብ የመጠቀም መብት (a non-exclusive, transferable, sub-licensable, royalty-free, worldwide license to use any IP content) ሰጥተውናል። ይህ የአይፒ ፈቃድ (‘IP License’) የሚቋረጠው የለጠፉትን የአይፒ ይዘት ወይም አካውንትዎን/አድራሻዎን ፈጽመው ካጠፉት (delete) ነው፤ ይህ የሚሆነው ግን የለጠፉዋቸው ይዘቶች ለሌሎች ከተካፈሉ እና እነርሱ ካላጠፉት ብቻ ነው።” በሌላ አነጋገር ፌስቡክ እኛ የምንለጥፈውን ማንኛውንም ነገር ባለቤትነት ይወስዳል፣ በማንኛውም በፈለገው መንገድ ሊጠቀምበትም ይችላል ማለት ነው።

የአሜሪካ መንግሥት የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ፌስቡክን እና ሌሎች የማኅበራዊ የመገናኛ መረብ ገጾችን ይከታተላል (monitor)፤ ሌሎች መንግሥታትም እንዲሁ እንደሚያደርጉ ይታመናል።

ለፌስቡክ የጥንቃቄ ጥቆማዎች!

 • በፌስ ቡክ የደኅንነት ጥበቃ አማራጮች (privacy settings) ተገቢውን ምርጫ ማድረጋችንን መላልሶ ማረጋገጥ! የፌስ ቡክ ተጠቃሚዎች ብዛት በጣም እየጨመረ የሚመጣ በመሆኑ እና ከተያያዥ ጫናዎች የተነሣ የምሥጢራዊነት ፖሊሲዎች በየጊዜው ይቀያየራሉ።

 • በፌስቡክ ላይ ሌሎች ሰዎችን “በጓደኝነት” ተቀበልን ማለት ከእነዚህ “ጓደኞቻችን” ጋራ ቀጥታ ግንኙነት ፈጠርን፣ መረጃዎቻችንን እና በፌስቡክ ላይ የምናደርገውን ነገር ሁሉ እንዲመለከቱ ፈቀድንላቸው ማለት ነው። ስለዚህ በፌስቡክ ልናምናቸው የምንችላቸውን ሰዎች ብቻ ጓደኛ ማድረግ የተመረጠ ነው።

 • ከአካውንታችን በወጣን (sign out) ቁጥር አካውንቱን ዲአክቲቬት (de-activate) ማለትም ከአገልግሎት ውጭ ማድረግ ያስፈልግ እንደሆነ ማሰቡም አይከፋም። ይህ ማለት አካውንቱን እኛ ወደአገልግሎት እስክንመልሰው ድረስ ማንም ሊያየው አይችልም ማለት ነው። ወደ ፌስቡክ ስንገባ (log in) አካውንቱን ወደ አገልግሎት እንመልሰዋለን (reactivate) ማለት ነው፤ ሁሉንም ነገር እንደነበረ እናገኘዋለን።

ስለፌስቡክ የምሥጢራዊነት/የደኅንነት መጠበቂያ አማራጮች በሚገባ ለመረዳት “'Controlling How You Share” የሚለው የድረ ገጹ ክፍል በጣም ጥሩ ምንጭ ነው http://www.facebook.com/privacy/explanation.php

ትዊተር (Twitter)

አገልግሎት (Function)፦ የሁኔታ ማሳወቂያ (ስታተስ አፕዴት)

ትዊተር ሲጀመር ዓላማው ከሞባይል ስልክ ወደ ኢንተርኔት ወቅታዊ መረጃዎችን መለጠፍ ነበር። 140 ቦታዎችን (የፊደል ቦታዎች) ብቻ የሚፈቅደውም ከዚህ በመነሣት ነበር። “የኢንተርኔት ኤስኤምኤስ” በመባል የሚጠራውም ለዚህ ነው። በትዊተር ሌሎች የሚሉትን/የሚጽፉትን ለመከታተል የምንፈልጋቸውን ተጠቃሚዎች “መከታተል” ('follow') እንችላለን። ሰዎቹን ልናውቃቸውም ላናውቃቸውም እንችላለን፤ ዋናው ነገር ሰዎቹ የሚለጥፉትን ጉዳይ መከታተል መፈለጋችን ነው። በተመሳሳይም “የሚከታተሉን” ሰዎች ጓደኞቻችን ላይሆኑ ይችላሉ፤ ይህም በአብሮነት ከሚመጣ አበሳ/ክስ (guilt by association) በተሻለ መልኩ ይከላከላል። ማንነትን ለመሰወርና ተለዋጭ ስሞችን ለመጠቀምም ምቹ ነው።

ትዊተር በአገልግሎት መስጠት ስምምነቱ እንዲህ ይላል፤ “ይህ ፈቃድ/ስምምነት ትዊት የሚያደርጓቸውን ነገሮች መላው ዓለም እንዲያገኘው እንድናደርግ ሥልጣን ይሰጠናል፤ ሌሎች ተጠቃሚዎችም ይህንኑ ማድረግ ይችላሉ። ሆኖም የእርስዎ የሆነው ሁሉ የእርስዎ ነው፤ የለጠፏቸው ይዘቶች ባለቤትነት የእርስዎ ነው።” ምንጭ http://twitter.com/tos)

ትዊተር ድረ ገጽ ነው። ይሁንና ብዙ ሰዎች “Twitter clients” በሚባሉ አፕሊኬሽኖች አማካኝነት ከዴስክቶፕ ኮምፒውተሮቻቸው ትዊተርን መጠቀም ይችላሉ። የትዊተር ተጠቃሚ (Twitter client) ከሆንን ከእውነተኛውና ደኅንነቱ ከተጠበቀው ድረ ገጽ ጋራ መገናኘቱን ማረጋገጥ አለብን።

የአሜሪካ መንግሥት የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ትዊተርን እና ሌሎች የማኅበራዊ የመገናኛ መረብ ገጾችን ይከታተላል (monitor)፤ ሌሎች መንግሥታትም እንዲሁ እንደሚያደርጉ ይታመናል።

ለትዊተር የአጠቃቀም ጥቆማዎች!

 • በትዊተር የሚለጠፍ ማንኛውም ነገር በቅጽበት ውስጥ በመላው ዓለም ሊታይ ይችላል። “እርስዎ ትዊት የሚያደርጉትን ነዎት፤ You are what you Tweet!”

 • በትዊተር የሚለጠፍ ማንኛውም ነገር በጊዜ ቅደም ተከተል ወደ ትልቁ የትዊቶች ባሕር ይገባል፤ ስለዚህ “በሚከታተሉን” ሰዎች ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ሊታይ ትችላል። ስሱ መረጃዎችን የምንለጥፍ ከሆነ የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርብናል። ትዊቶችን መጠበቅ ማለት “የሚከታተሉን” ሰዎች ብቻ እንዲያዩዋቸው ማድረግ ማለት ነው። ሆኖም “የሚከታተሉን” ሰዎች መልሰው ሊለጥፏቸው ወይም ሪትዊት (retweet) ሊያደርጓቸውና ለሕዝብ ሁሉ ሊደርሱ እንደሚችሉ መዘንጋት የለብንም።

 • መንግሥትን ወይም ባለሥልጣናትን የሚተቹ ነገሮችን ትዊት የምናደርግ/የምንለጥፍ ከሆነ ማንነታችንን ደብቀን በተለዋጭ ስሞችና ማንነቶች መጠቀም ይመረጣል።

ዩትዩብ (YouTube)

አገልግሎቶች (Functions):- ቪዲዮዎችን እና ሌሎች የኢንተርኔት ይዘቶችን ማካፈል

የዩትዩብ ባለቤት ጉግል (Google) ነው። ዩትዩብ ቪዲዮዎችን በሚልዮን ለሚቆጠሩ ተጠቃሚዎቹ ለማካፈል በጣም ምቹ መንገድ ነው። ነገር ግን የጉግል አስተዳዳሪዎች የለጠፍነውን ቪዲዮ በተለያየ ምክንያት “አግባብነት/ተቀባይነት የሌለው”( objectionable) መሆኑን ካመኑበት ሊያጠፉት ይችላሉ። ይህም ዩትዩብ ቪዲዮዎቻችንን ለማስቀመጥ አስተማምኝ አማራጭ እንዳይሆን ያደርገዋል። በተጨማሪም ጉግል ከተለያዩ ወገኖች በሚመጣበት ጫና እና ድረ ገጹ ሳንሱር እንዳይደረግ ለመጠበቅ ሲል ቪዲዮዎችን ከገጹ እንደሚያጠፋ ይታወቃል። ስለዚህ ሰዎች ቪዲዮዎቻችንን እንዲያዩልን ከፈለግን ቅጂውን ዩትዩብ ላይ መጫን (upload) እንችላለን፤ ነገር ግን ብቸኛ ቅጂያችንን ለጥንቃቄ በሚል ዩትዩብ ላይ ማስቀመጥ የለብንም።

ጉግል በገጹ ላይ የሚጫኑ (uploaded) ቪዲዮዎችን የጫነውን ተጠቃሚ ስም እና ያለበትን ቦታ ይጽፋል። ይህም የጫኑትን ሰዎች ለመከታተል ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል። በዩትዩብ ላይ የምንጭነው ቪዲዮ የባለቤትነት መብት የራሳችን ነው፤ ነገር ግን ዩትዩብ ላይ በመጫን ለጉግል የማሰራጨት ፈቃድ እንደሰጠነው ይቆጠራል።

እ.አ.አ. ከመስከረም 2010 ጀምሮ ዩትዩብ በቻይና፣ በኢራን፣ በሊቢያ፣ በቱኒዚያ እና በቱርክሜኒሰታን ታግዷል። ይህ መጻሕፍ በሚታተምበት ወቅት በእነዚህም ሆነ በሌሎች አገሮች ያለው ሁኔታ ተቀይሮ ሊሆን ይችላል።

የዩትዩብ የጥንቃቄ ጥቆማዎች###

 • የሌሎች ሰዎችን ቪዲዮ ያለፈቃዳቸው አንጫን። ፈቃደኛ ቢሆኑ እንኳን ቪዲዮውን ከመጫናችን በፊት ድርጊቱ ሊያስከትል የሚችለው አደጋ ይኖር እንደሆነ መላልሰን ማሰብ አለብን።

 • ምንግዜም በጉግል/ዩትዩብ በመጫን ለሌሎች የምናካፍለውን ቪዲዮ መጠባበቂያ ቅጂ ማስቀመጥ ይኖርብናል።

 • የተወሰኑ ሰዎች ብቻ እንዲያዩት የምንፈልገው ቪዲዮ ሲኖር ይህን ለማድረግ የሚያስችለውን ምርጫ (private setting) መምረጥ አለብን።

ፍሊከር (Flickr)

አገልግሎት (Functions)፡ ፎቶ/ቪዲዮ እና የኢንተርኔት ይዘቶችን ማጋራት

የፍሊከር ባለቤት ያሁ! (Yahoo!) ነው።

በፍሊከር ላይ የለጠፍነው ነገር ባለቤቶች እኛው ነን፤ አልፎም የፈጠራ ባለቤትነት እና የመጠቀም ፈቃድ (creative commons licenses or copyright) ልንፈጥርላቸው እንችላለን። ሆኖም ፎቶዎችን እና ቪዲዮዎችን ስንለጥፍ ለያሁ! የማሰራጨት ፈቃድ እንደሰጠነው ይቆጠራል።

ፍሊከር የተለያዩ የመለያ ፈቃድ (licensing attribution) አይነቶችን የሚያቀርብ በመሆኑ ለተለያየ ዓለማ የሚውሉ ምስሎችን በቀላሉ ፈልጎ ለማግኘት እና ከምንፈልጋቸው ወገኖች ጋራ ምስሎችን ለመጋራት በጣም የተመቸ ነው።

የፍሊከር የጥንቃቄ ጥቆማዎች

 • ፍሊከር በካሜራችን የሚመዘገቡ ስውር መረጃዎችን (metadata) (ለምሳሌ ቀን፣ ሰዓት፣ ጂፒኤስ ስፍራ፣ የካሜራ ሞዴል ወዘተ) ገልጦ እንደማያሳይ ማረጋገጥ

 • ፈቃዳቸውን ሳናገኝ የሰዎችን ፎቶ በፍሊከር ለሌሎች አለማካፈል፤ በተጨማሪም ከምስሉ ጋራ የምናያይዘው የፈቃድ አይነት ባለምስሎቹ የሚስማሙበት መሆኑን ማረጋገጥ

የአሜሪካ መንግሥት የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ፍሊከርን እና ሌሎች የማኅበራዊ የመገናኛ መረብ ገጾችን ይከታተላል (monitor)፤ ሌሎች መንግሥታትም እንዲሁ እንደሚያደርጉ ይታመናል።

ማስታወሻ፤ አማራጭ መሣሪያዎች (Alternative Tools)##

በዚህ ምእራፍ የቀረቡት በስፋት ታዋቂ የሆኑት እና በስፋት ጥቅም ላይ የዋሉት ማኅበራዊ መረቦች/ገጾች መሣሪያዎች (tools) ናቸው። መንግሥታት አፈና መፈጸም ሲጀምሩ በቅድሚያ የሚወስዱት እርምጃ እነዚህን ድረ ገጾች ማገድ ነው። በተጨማሪም እነዚህ መሣሪያዎች በግል ኩባንያዎች ባለቤትነት ስር የሚገኙ እንደመሆናቸው አስፈላጊ ሲሆን ለመንግሥት ጫና መገበራቸው እና ሳንሱር ማድረጋቸው አይቀርም። ስለዚህም የዲጂታል ደኅንነትን እና የመብት አቀንቃኞችን ከግምት በማስገባት የተፈጠሩትን ዲያስፖራ (Diaspora) (http://joindiaspora.com) እና ክራብግራስ (Crabgrass) (http://we.riseup.net) የመሳሰሉትን አማራጮች መመልከት ይመከራል።